
AMN ግንቦት 16/2017
የኢትዮዽያ መንግስት ለደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን እና የአጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪርና ምክትል ፕሬዚዳንቱ ቤንጃሚን ቦልሜል ጋር ተወያይተዋል።
የልዑካን ቡድኑም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተላከ መልዕክት ለደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር አድርሷል።
በውይይቱም፥ የደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት ከኢትዮዽያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የተሳሰረ በመሆኑ፥ የኢትዮዽያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለኢዜአ የላከው መረጃ ያስረዳል።
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንትና ምክትላቸውም ኢትዮዽያ ከጅምር ጀምሮ እስካሁን የዘለቀና የማይናወጥ ድጋፍ እያደረገች መቆየቷን በማውሳት ምስጋናና አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር፥የኢትዮጵያ መንግስት ለሀገራቸው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።
የልዑካን ቡድኑ የደቡብ ሱዳን ቆይታውን በማጠናቀቅ ትናንት ማምሻውን ወደ ሀገር ተመልሷል።