AMN – ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በትውልድ ቅብብሎሽ ለሉዓላዊነት የተከፈለ መስዋዕትነት እና ኅብረብሄራዊ አንድነትን የሚያሳይ ምልክት መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ታየ አጽቀሥላሴ ገለጹ፡፡
የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ17ኛ ጊዜ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተከብሯል፡፡
በመርሐግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ፕሬዝደንት ታየ አጽቀሥላሴ፣ ሰንደቅ ዓላማ የብሄራዊ ህብረታችን እና የሉዓላዊነት መገለጫ ነው ብለዋል፡፡
ሰንደቅ ዓላማ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ከፍለው በክብር አስጠብቀው ያስረከቡን እና በልባችን ታትሞ የቆየ የአሸናፊነት የነጻነት አርማ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዓመታት ነጻነቷንና ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ታፍራና ተከብራ የቆየች ታላቅ ሀገር ናት ያሉት ፕሬዝደንቱ በመንግስታዊ አስተዳደር ስርዓት ረዥም ዓመታት ካስቆጠሩ ቀዳሚ ሀገራት ተርታ እንደምትቀመጥ ጠቁመዋል፡፡
የሰንደቅ ዓላማ ታሪክ ከሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ጋር በእጅጉ የተቆራኘና የተሳሰረ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ ብሄራዊ መገለጫ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካዊያን እና ለመላው ጥቁር ህዝቦች ዘንድ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው የነጻነትና የእኩልነት አርማ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ለሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር በመስጠት በዓሉን ትርጉም ባለው መልኩ ማክበር ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
በዓሉ ሲከበር ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ እና በሰንደቅ ዓላማ ስር በጋራ በመሰባሰብ ሊሆን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን በደማቸው ነጻነቷን አስጠብቀው ያቆዯትን አገር በእውቀትና በጉልበት በማልማት ያለብንን የዘመናት እዳዎች ወደ ሀብት መቀየር ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
ሉዓላዊነት በዘለቄታነት ሊከበር የሚችለው ሀገራችንን ከልመና ነጻ በማውጣት ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ ያሁኑ ትውልድም በተሰማራባት ዘርፍ ሁሉ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ መረባረብ ይጠበቅበታል በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በሰፊና ሁሴን