AMN-የካቲት 19/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ተቀማጭ 1.54 ትሪሊየን ብር መድረሱን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ገለጹ።
ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት ከኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (ኢአይኤች) የሥራ ኃላፊዎች ጋር በነበረው የግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ነው።
አቶ አቤ የባንኩ አጠቃላይ የሥራ አፈፃፀም መልካም መሆኑን ጠቅሰው፣ በበጀት ዓመቱ እስከ የካቲት 16 ቀን 2017 ድረስ የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ ብዛት ከ350 ቢሊየን ብር በላይ መድረሱን አመልክተዋል።
በዚህም የባንኩ ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ1.54 ትሪሊየን ብር መሻገሩን ጠቁመዋል።

አጠቃላይ በባንኩ ከተፈጸሙ የገንዘብ ግብይቶች 84.5 በመቶ የሚሆነው በዲጂታል የክፍያ አማራጮች የተፈጸሙ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህም አበረታች የሚባል ነው ብለዋል።
ባንኩ የአገልግሎት ጥራቱንም ይበልጥ ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የብድር አገልግሎት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የባንኩ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በዘንድሮው በጀት ዓመት ጠቅላላ የብድር መጠን ወደ 1.35 ትሪሊየን ብር ማደጉን ጠቁመዋል።
በቅርቡም አዳዲስ የብድር ዓይነቶችን በተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ለባንኩ ደንበኞች በማስተዋወቅ የብድር ተደራሽነቱን ለማሳደግ እንደሚሰራ መግለጻቸውን የባንኩ መረጃ ያመለክታል።