የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ጠቅላላ ጉባዔ በሀዋሳ እየተካሄደ ነው

You are currently viewing የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ጠቅላላ ጉባዔ በሀዋሳ እየተካሄደ ነው

AMN-ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ጠቅላላ ጉባዔ እና የተሞክሮ ልምድ ልውውጥ መድረክ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የከተማ ልማትና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን፣ ከ100 የሚበልጡ ከተሞች አስተዳደሮች ከንቲባዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የትብብር መድረኩ በከተሞች የሚከናወኑ መሰረተ ልማቶችን በማጠናከር ከተሜነትን ለማስፋፋትና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የሚያግዙ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት መሆኑ ተገልጿል።

እንዲሁም ከንቲባዎችና ሌሎች የአመራር አባላት ልምድ በመለዋወጥ በከተሞች የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችል አቅም የሚፈጥሩበት መሆኑን ተመላክቷል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባዔው በኢትዮጵያ ከተሞች ማህበራዊና ኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ ጥናት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበትና የሀዋሳ ከተማ የኮሪደር ልማት የመስክ ምልከታ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

በተጨማሪም የተሻሻለው የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ መተዳደሪያ ደንብ እንደሚጸድቅና በከተሞች የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቋቋም በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ሰነድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት እንደሚደረግበትም መመላከቱን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ በ2001 ዓ.ም 19 ከተሞችን በአባልነት በማቀፍ የተቋቋመ ሲሆን፤ አሁን ላይ 101 ከተሞች የትብብር መድረኩ አባል እንደሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review