የኢትዮጵያ የስንዴ ልማት ስኬት አፍሪካ በምግብ ራሷን እንደምትችል ማረጋገጫ ነው- ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

You are currently viewing የኢትዮጵያ የስንዴ ልማት ስኬት አፍሪካ በምግብ ራሷን እንደምትችል ማረጋገጫ ነው- ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

AMN – የካቲት 5/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ያስመዘገበችው ስኬት አፍሪካ በምግብ ራሷን እንደምትችል ማረጋገጫ ነው ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።

ዓለም አቀፍ የመስኖ ልማትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ምርታማነት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የአየር ንብረት ለውጥና የምግብ ዋስትና ችግር እየተባባሰ መሆኑን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጭነት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ማህብረሰብ አቀፍ የግብርና ልማት ሽግግርን እየመራች ነው ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምን ታሳቢ ያደረጉ የምግብ ምርታማነት ሥራዎችን እያከናወነች መሆኗን ጠቅሰው፥ ለአብነትም የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብርን ጠቅሰዋል።

በዚህ መርሐግብር 40 ቢሊዮን ችግኝ መትከላችን ብቻ የደን ሽፋንን ከማሳደጉም በላይ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ ዋስትናቸውን እያረጋገጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሌላኛው የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ኢኒሼቲቭ የስንዴ ልማት መሆኑን ጠቅሰው፥ በዚህም ከውጭ የሚገባን ስንዴ በማቆም የስንዴ ምርት ፍጆታዋን በራሷ አቅም ማምረት ችላለች ብለዋል።

ይህም አፍሪካ ራሷን መመገብ እንደምትችል ማረጋገጫ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ለመስኖ፣ ለሜካናይዜሽንና ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የግብርና ስርዓቶች ትኩረት በመስጠት የምግብ ሉዓላዊነቷን ታረጋግጣለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋትን በመጀመር በቤተሰብ ደረጃ የተመጣጠነ የምግብ ስርዓትን የሚያረጋግጡ የወተት፣ የእንቁላል፣ የማርና ሌሎችንም ምርቶች ላይ በማተኮር ውጤታማ ስራዎችን እየሰራች መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አፍሪካም ሌማቷን መሙላት የሚያስችላት አቅም አላት ያሉት ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ተሞክሮ ለአህጉሪቱ የሚተርፍ እንደሆነም አንስተዋል።

በመስኖ ልማት መርሀ ግብሩ አርብቶ አደሮች ጭምር እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቶቻችን የምግብ ዋስትናንና የማይበገር የግብርና ስርዓት መገንባትን ዓላማ ያደረጉ ናቸው ብለዋል።

አፍሪካውያን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለመስኖ ልማት፣ ለግብርና ኢንቨስትመንት፣ ለቴክኖሎጂና ለመረጃ ጥራት ትኩረት እንዲሰጡም መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አፍሪካውያን በጋራ ከሰሩ ርሃብን ማስወገድ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በብቃት መቋቋምና የትውልዱን የብልፅግና መሻትን ማሳካት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review