
AMN ህዳር 20/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በጥቂት ወራት ውስጥ አስደናቂ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑን እያየን ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የዴንማርክ ምክትል ሚሲዮን መሪ ሰባስቲያን ሉካስ ባች ተናገሩ።
ለረጅም ዘመናት የዘለቀው የኢትዮ- ዴንማርክ የሁለትዮሽ ግንኙነትም በልማትና በተለያዩ የትብብር መስኮች ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ምክትል ሚሲዮን መሪው እንደገለጹት ሁለቱ ሀገራት የአየር ፀባይ ለውጥን ለመከላከል፣ ለአየር ፀባይ ለውጥ የማይበገር ብሎም የአየር ፀባይ ለውጦችን የሚቋቋም ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በጋራ እየሰሩ ነው።
በበርካታ ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰሩ መሆኑን በመጥቀስ ለማሳያነት የግብርና እና የኃይል ዘርፉን አንስተዋል፡፡
የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለው አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገትም አስደናቂና በማሳያነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በጥቂት ወራት ውስጥ አስደናቂ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑን እያየን ነው ሲሉም አክለዋል።
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ግብርናን በመከተል፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና በተለይም የኃይል ተደራሽነትን በማስፋት ጥሩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ ዴንማርክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ትብብር አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ የብዙዎችን ህይወት ለመለወጥ እያገዘ ያለውን የሴፍቲኔት ፕሮግራም ውጤታማ ለማድረግ የዴንማርክ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።