የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነው ግብርና እመርታ እያሳየ ነው-ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

AMN – ታህሳስ 1/2017 ዓ.ም

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከታንዛኒያን ልዑካን ቡድን ጋር በአሁናዊ የኢትዮጵያ ግብርና ቁመና ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ባስመዘገበቻቸው ስኬቶች ዙሪያ ለታንዛኒያ ልዑካ ቡድን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በሁለትዮሽ ውይይቱ፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድ ለተለዩ ቁልፍ ተቋማት (ግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና አይሲቲ) ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ለሀገሪቱ 1/3ኛ አጠቃላይ ዕድገት፣ 2/3ኛ ኤክስፖርት እንዲሁም 65 በመቶ የሥራ ዕድል ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነው ግብርና እመርታ እያሳየ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ የአጋር አካላትንና የፕሮጀክቶችን ድጋፍ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር “አንድ ዕቅድና አንድ ሪፖርት” እንዲኖራቸው እየተደረገ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ከገጠሩ ክፍል ባሻገር የከተማ ግብርና ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑንም ዶ/ር ግርማ ጠቁመዋል፡፡

የሕብረተሰቡን የእንስሳት ተዋጽኦ ፍላጎት ለማሟላት ብሔራዊ ኢኒሼቲቭ ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው የወተት፣ ዶሮ፣ ማር እና ዓሳ መንደሮችን በየአካባቢው በመመስረት ውጤታማ መሆን ችለናል ብለዋል፡፡

እነዚህን መንደሮች ማስፋፋት ከውጭ የሚገባውን የዶሮ ስጋ ለማስቀረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ አባላት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን ለውጥ አድንቀው የሁለትዮሽ ትብብሩ አንዱ ከሌላው ልምድ እንዲቀስም የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የታንዛኒያ ልዑካን ቡድን አባላት በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉ ሲሆን በእንስሳት ልማቱ የተገኙ ተሞክሮዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review