የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ግዥን ጨምሮ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያዎችን በማካሄድ ከ254.6 ሚሊየን ብር በላይ በማዋጣት ገቢ ማድረጉን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ቃል-አቀባይ ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ቸኮል፣ በዋና መሥሪያ ቤቱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አመራርና አባላት የግድቡ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ለ14 ዓመታት ያለማቋረጥ 24/7 ሰዓት የግድቡ ሥራ ለሰከንድም ሳይቋረጥ የሠራተኞች ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ እየተጠበቀ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
ቃል-አቀባዩ አክለውም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አመራርና አባላት የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ሁለንተናዊ ደኅንነት ከመጠበቅ ባሻገር እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የዜግነት ኃላፊነትን ለመወጣት የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን በማካሄድ፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዋንጫን በክብር በጠቅላይ መምሪያዎች በማዘዋወር እና መላዉ ሠራዊቱ በተደጋጋሚ ከደምወዙ በማዋጣት በቦንድ ግዥ በጠቅላላው ከ254.6 ሚሊየን ብር በላይ አሰባስበው ገቢ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ በሰፊዉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የቱሪስት ፍሰቱም በዛው ልክ ስለሚጨምር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተግባርና ኃላፊነት ዘርፈ ብዙ እየሆነ ስለሚመጣ ከወዲሁ በዘመናዊ ጀልባ የታገዘ የተጠናከረ ጥበቃ ለማድረግ ፖስታል ጋርድ ፖሊስ አደራጅቶ ወደ ተግባር ለመግባት ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን መገለጹን ከፌደራል ፖሊስ ማህበራዊ የትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡