የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነትና ትብብርን የበለጠ ለማጠናከር ከሩዋንዳ ብሔራዊ ፖሊስ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

You are currently viewing የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነትና ትብብርን የበለጠ ለማጠናከር ከሩዋንዳ ብሔራዊ ፖሊስ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

AMN – ታኀሣሥ 7/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነትና ትብብርን የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ከሩዋንዳ ብሔራዊ ፖሊስ ኢንስፔክተር ጀነራል ፌሊክስ ናሙሆራንዬ ጋር በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት ተፈራርመዋል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እና ኢንስፔክተር ጀነራል ፌሊክስ ናሙሆራንዬ ስምምነቱን አስመልክተው በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት ሽብርተኝነት፣ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ መረጃ በመለዋወጥ በጋራ ለመከላከል መስማማታቸውን ገልፀዋል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ፣ በሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት ያሉ የቴክኖሎጂ እና ሌሎች አቅሞችን በመጠቀም በተለይ በአንጋፋው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ እና በሩዋንዳ ብሔራዊ ፖሊስ አካዳሚ ወጣት የፖሊስ ኦፊሰሮችን ለማሰልጠን እና ልምድ ለመለዋወጥ መግባባታቸውን በመግለጫው አንስተዋል፡፡

አያይዘውም የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ ትብብር መድረክን በጋራ ለማጠናከር እና ከምስራቅ አፍሪካም ባለፈ እንደ አፍሪፖል ያሉ ተቋማትን ለማጠናከር በጋራ ለመስራት መነጋገራቸውንም ገልፀዋል።

በቀጣይም በ2025 በሚካሄደው የኢንተርፖል ፕሬዚዳንት ምርጫ ላይ እንደ አፍሪካ እጩ ተወዳዳሪ በጋራ ለማዘጋጀት፤ የሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት ትብብር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እና ተቀናጅተው ለመሥራት መስማማታቸውን በመግለጫው አንስተዋል፡፡

ስምምነቱ በቅርቡ ወደ ተግባር እንዲቀየር ከሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት የተቀናጁ ቴክኒካል ቲም መደራጀቱን ገልፀው የቡድኑ አባላት በቅርቡ ተገናኝተው ስምምነቱ ወደ ተግባር የሚቀየርበትን ዕቅድ አዘጋጅተው ወደ ተግባር እንደሚገባ በመግለጫው አመላክተዋል፡፡

የሩዋንዳ ብሔራዊ ፖሊስ ኢንስፔክተር ጀነራል ፌሊክስ ናሙሆራንዬ በበኩላቸው፣ ስለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በተፈረመው ስምምነት የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር እንዲጠናከር እና እንዲተገበር የሩዋንዳ ብሔራዊ ፖሊስ ታማኝ አጋር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ማዕቀፉ የሁለቱ ሀገራት ደኅንነትን ለማረጋገጥ አስተዋፅኦ ከማድረጉም ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ብሎም ለዓለም የድርሻውን እንደሚያበረክት መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review