የኢትዮጵያ ፖሊስ የተመሰረተበት 116ኛው በዓል ከሚያዝያ 19 እስከ 26 ቀን 2017 ዓም በተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚከበር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ቸኮል በሰጡት መግለጫ፥ ፖሊስ የተመሰረተበትን ቀን በተለያዩ መርሃግብሮች ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል።
ከሚያዝያ 19 እስከ 25/2017 ዓ.ም ድረስ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ፖሊስ ተቋማት የሚሳተፉበት ስፖርታዊ ውድድር እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ውድድሩ የሚካሄደው በስድስት ዓይነት ዘርፎች ሲሆን ውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ሀገራት ወደ አዲስ አበባ በመግባት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ሚያዝያ 23/2017 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም ለግማሽ ቀን የሚቆይ ሲምፖዚየም ምሁራን እና የፖሊስ አመራሮች እንዲሁም የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።
እንደ ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ገለጻ፥ ፖሊስ የደረሰበትን ደረጃ የሚያስቃኝ አውደ ርዕይም የሚካሄድ ይሆናል።
ሚያዚያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ደግሞ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የፖሊስ ተቋማት እንዲሁም የብሪክስ አባል ሀገራት አመራሮችና ተወካዮች በሚገኙበት የማጠቃለያ በዓል በመስቀል አደባባይ እንደሚከበር ተናግረዋል።