AMN – ጥር 13/2017 ዓ.ም
የኢፌዴሪ አየር ኃይል ግምቱ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የተለያዩ አልባሳት፣ ቁሳቁሶችንና የምግብ እህል አይነቶችን ጨምሮ ማዕድ የማጋራት ድጋፎችን ለመቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል አከናውኗል፡፡
የአየር ሀይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳን ጨምሮ ከክፍሉ የተውጣጡ አመራርና አባላቱ ማዕከሉን ተዘዋውረው ጉብኝተዋል።
ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ ሠራዊቱ የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚጠብቅና ካለው ላይ በማካፈል ህዝባዊ ሰራዊት መሆኑን እያረጋገጠ የመጣ መሆኑን በመግለጽ የአየር ሀይሉ አባላት ዛሬ በነበረው የመቆዶንያ በጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍና ማዕድ የማጋራት ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይነትም መርጃ ማዕከሉንም ይበልጥ ለማገዝ በገቢ ማሰባሰቡ ሂደት ሠራዊቱ ባለበት ቦታ ሁሉ በማስተባበር ወደፊት በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የመቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መስራች ቢንያም በለጠ፣ አየር ሀይሉ ላደረገው ድጋፍ ሠራዊቱ ላሳየው ወገንተኝነት በመርጃ ማዕከሉ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
አየር ሀይሉ ከተሰጠው ሀገራዊ ተልዕኮ የወገን ደራሽነቱን ያረጋገጠበት ተግባር መሆኑን በማንሳት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡