
AMN ህዳር 20/2017 ዓ.ም
“የተከበረች ሀገር የማይደፈር አየር ኃይል” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኘውን 89ኛውን የአየር ኃይል ቀን የምስረታ በዓልን በማስመልከት የኢፌዴሪ አየር ኃይል ያዘጋጀው የአቭዬሽንና የተለያዩ ወታደራዊ ትጥቆች ኤግዚቪሽን በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በይፋ ተመርቆ ተከፍቷል።
በኢፌዴሪ አየር ኃይል ፣በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ የተመረቱ እንዲሁም ደግሞ አፕግሬዲንግና ኦቨርሆል ተደርጎላቸው የሠራዊታችንን የማድረግ አቅም ከፍ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ዘመናዊ ወታደራዊ ትጥቆች በኤግዚቢሽኑ ላይ ለዕይታ ቀርበዋል።
ትጥቆቹ የኢትዮጵያን አየር ኃይል እና የመከላከያ የኢንዱስትሪ ተቋማትን የፈጠራ አቅም ያሳዩ ከመሆኑም ባሻገር በራስ አቅም ጠንካራ ተቋም ለመገንባት የተያዘውን ዕቅድ በአጭር ጊዜ ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑ ተገልጿል።
በኤግዚቪሽኑ ላይ የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች፣ ወታደራዊ አታሼዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ጀኔራል መኮንኖችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።