AMN – ጥር 9/2017 ዓ.ም
የእስራኤል የመካላከያ ሚኒስቴር በሃማስ የታገቱ እስራኤላውያንን በእስራኤል እስር ቤት ባሉ ፍልስጤማውያን ለመለዋወጥ እና ለ15 ወራት የዘለቀውን ጦርነት ለመጀመሪያዎቹ ስድስት ሳምንታት ለማቆም የተደረሰውን ስምምነት አጽድቋል፡፡
ስምምነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ በመዘግየቱ፣ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በእስራኤል እና ሃማስ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ስምምነቱን አደናቅፎት ይሆናል በሚል ስጋት አጭሮ እንደነበር ተነግሯል፡፡
ለ42 ቀናት በሚቆየው በዚህ ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ፣ ሃማስ፣ ሴት ወታደሮችን እና ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸውን ጨምሮ 33 ታጋቾችን ለመልቀቅ ተስማምቷል።
በምላሹም እስራኤል በሃማስ ለተለቀቁ እያንዳቸው ሴት የእስራኤል ወታደሮች፣ 50 የፍልስጤም እስረኞችን እንዲሁም በሌሎች ሴቶች ደግሞ 30 እስረኞችን የምትለቅ ይሆናል ።
ውሳኔው የመጨረሻ ይሁንታን እንዲያገኝ በቀጣይ ወደ ጠቅላላ ጉባኤ የሚቀርብ ሲሆን፣ በስምምነቱ መሠረትም የፊታችን እሁድ የመጀመርያዎቹ ታጋቾች እና ታሳሪዎች እንደሚለቀቁ ተመላክቷል፡፡
የእሥራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሁንም በስምምነቱ አንዳንድ ክፍሎች ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ለመስማት ዝግጁ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን በሰፊው ጣልቃ ይገባል ተብሎ እንደማይጠበቅ መገለጹን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል።