የናይጄሪያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የእግር ኳስ ተጫዋቿ አሲሳት ላሚና ኦሾላ ሻምፒዮንስ ሊግን ያሸነፈች የመጀመሪያዋ ሴት አፍሪካዊ ኮከብ ተጫዋች ነች። እንደዚሁም በሦስት የተለያዩ የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ ጎል ያስቆጠረች የመጀመሪያ ናይጄሪያዊ እግር ኳስ ተጫዋችም ናት፡፡ ይሁንና እነዚህና ሌሎች ወደ ኋላ ላይ የምንገልጻቸው የተጫዋቿ ስኬቶች የተገኙት አልጋ በአልጋ በሆነ የህይወት መንገድ አልነበረም፡፡ ከዓመት በፊት ‘ዓለም አቀፍ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ፌዴሬሽን’ የሴቶች እግር ኳስን አስመልክቶ ያወጣው መረጃም የሚያመላክተው ሴቶች በምን አይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ እየተሳተፉ እንደሆነ ነው።
ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች በአስቸጋሪ የሥራ ሁኔታ፣ ፍትሃዊ ያልሆነ ክፍያ እና ወሲባዊ ጥቃትን ጭምር እንደሚያስተናግዱ እና 29 በመቶ የሚሆኑት ሴት ተጫዋቾች ደግሞ ከብሔራዊ ቡድናቸው ክፍያም እንደማይሰጣቸው የፌዴሬሽኑ ሪፖርቱ ያትታል፡፡ ይባስ ብሎም የእግር ኳስ ቡድን የአሰልጣኝነት ሥራዎች ውስጥ 80 በመቶው በወንዶች የተያዙ ናቸው። የሆነው ሆኖ በብዙ ፈተና ውስጥ አልፈውና የታሰበውን ያህልም ባይሆን የሴቶች ስፖርታዊ ተሳትፎ ቀስ በቀስ እያደገ ስለመምጣቱ አያከራክርም፡፡ ለዚህም በውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው ለስኬት የበቁ ሴት ስፖርተኞችን መመልከት አስፈላጊ በመሆኑ በዚህ ጽሑፍ ጥቂቶቹን እናወሳለን፡፡
እግር ኳስን ከሐዋሳ ከተማ ከጀመረች በኋላ በመቀጠል በደደቢት፣ በአዳማ እና ከሀገር ውጪ በሆላንድ ክለቦች የሙከራ እና በማልታው ቢርኪርካራ ደግሞ የተሳካ ቆይታን አድርጋ በኋላም ወደ አሜሪካ ያቀናችው ሎዛ አበራ አንዷ ነች፡፡ በእግር ኳስ ህይወቷ የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እና የምርጥ ተጫዋችነት ክብርን በተደጋጋሚ ያገኘቸው አጥቂዋ ሎዛ ባደገችበት ሠፈር ካሉ ወንድ እኩዮቿ ጋር እየተጋፋች ኳስን ስትጫወት እንዳደገች የህይወት ታሪኳ ያስረዳል፡፡
የሎዛ ፕሮፌሽናል ኳስ ተጫዋችነት ጉዞ የተጀመረው የከንባታ ዞንን ወክላ ስትጫወት ባይዋት መልማዮች አማካይነት ነው። ብዙም ሳትቆይ ሎዛ የሐዋሳ ሴቶች እግር ኳስ ቡድንን ተቀላቀለች። ከሐዋሳ ጋር ዋንጫ ባታነሳም እዚያ በቆየችባቸው ሁለት ተከታታይ ዓመታት የክለቡ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ነበረች። ሐዋሳን ከለቀቀች በኋላ በደደቢት አራት ዓመታትን ያሳለፈችው ሎዛ በሁሉም ዓመታት በተከታታይ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ነበረች። ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ደግሞ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን ሆናለች፤ አሁን ላይ ወደ አሜሪካ በማቅናት የእግር ኳስ ተጫዋችነት ፊርማዋን በዋሽንግተን ዲሲ ለሚገኘው ዲሲ ፓወር ኤፊሲ የምትጫወተው ሎዛ ይህም የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ሴት ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች ሆናለች፡፡
ሁሉም ነገር ለወንዶች ቅድሚያ በሚሰጥበት ወቅት የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ውጤታማ መሆኑ ከዚህም በላይ መሄድ አንደሚቻል ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ የተናገረችው ሎዛ በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ እንዲያድግ ከተፈለገ ሁሉም ክለቦች ከወንዶች እኩል የሆነ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ትላለች፡፡ መጫወቻ ሜዳ፣ ትራንስፖር፣ የላብ መተኪያ እና ሌሎች መሰረታዊ ነገሮች ሳይሟሉ ለብሔራዊ ቡድን እና ለክለቦች ሲጫወቱ ነበር የምትለው ሎዛ አሁን ብዙ ነገሮች እየተሻሻሉ መሆኑን ትናገራለች። ወጣት ሴቶች ስኬታማ እግር ኳስ ተጫዋች ለመሆን ከጎጂ ነገሮች ራስን ማራቅ፣ አዋዋልን መምረጥ፣ ተስፋ አለመቁረጥ፣ ዓላማን በሚገባ መረዳት እና ሌሎች ጽናት የሚጠይቁ ፈተናዎችን መቋቋም እንዳለባቸውም ትመክራለች።

በስፖርቱ ዓለም በአርኣያነት የምትጠቀሰው ሌላኛዋ እንስት ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ናኦሚ ግርማ ነች፡፡ ወላጅ አባቷ ግርማ ወርቁ በካሊፎርኒያ “ማለዳ ሶከር ክለብ” የሚባል ቡድን አቋቁመው አዳጊዎችን ያሰለጥኑ የነበሩበት የአዳጊ ቡድን ውስጥ ነበር የአሁኗ ታዋቂ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ተጫዋች ወጣት ናኦሚ ግርማ የእግር ኳስ ስኬት ጥንስስ የሚጀምረው፡፡ ዘ ዩኤስ ሰን የተሰኘው መገናኛ ብዙሃን ስለ ናኦሜ ባስነበበው መረጃ ለዚህ ደረጃ እንድትደርስ ትልቁን ሚና የተጫወተው አባቷ አቶ ግርማ እንደሆነና እሷ ገና አዳጊ እያለች አባቷ ያቋቋሙት ክለብ መሰረት እንደሆናት ትናገራለች፡፡
የተከላካይ ክፍል ተጫዋቿ በፈረንጆቹ 2020 የአሜሪካ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጥሪ የደረሳት ሲሆን፣ አሜሪካ ኡዝቤኪስታንን ባሸነፈችበት ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ 90 ደቂቃ ተሰልፋ መጫወት ችላለች፡፡ በ2020 በሰሜን፣ ማዕከላዊና ካሪቢያን ሀገራት ውድድር ላይ በተሳተፈውና አሰልጣኝ ላውራ ሃርቪ በምትመራው የአሜሪካ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሸናፊ ሲሆን ቡድኑን በአምበልነት መርታለች። አሁን ላይ እየተጫወተችበት የነበረውን የአሜሪካው ሳንዲያጎ ዌቭ ክለብን ለቅቃ ወደ እንግሊዙ ክለብ ቸልሲ በማቅናት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እየተጫወተች ትገኛለች፡፡
በሴቶች እግር ኳስ ክብረ ወሰን 900 ሺህ ፓውንድ በሆነ ዋጋ ለቼልሲ የፈርመችው የ24 ዓመቷ አሜሪካዊቷ ተከላካይ በአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር እስከ 2029 ከሰሜን ለንደኑ ክለብ ጋር የሚያቆያትን ፊርማ አኑራለች። ናኦሚ ያለፈው ዓመት የቢቢሲ ስፖርት የዓመቱ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ዕጩ እንደነበረች አይዘነጋም። በፈረንጆቹ የዘመን ቀመር በ1994 የተወለደችው አሲሳት ላሚና ኦሾላ ናይጄሪያዊ ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ክለብ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ናት፡፡ በአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ስድስት ጊዜ ሪከርድ በማሸነፍ ከምንጊዜውም የአፍሪካ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል አንዷ ነች።
ኦሾላ ከዚህ ቀደም ለእንግሊዝ ክለቦች አርሰናል እና ሊቨርፑል፣ የቻይናው ዳሊያን ክለብ እና የናይጄሪያ ክለቦች ሪቨርስ አንጀለስ እና ኤፍሲ ሮቦ ተጫውታለች። እ.ኤ.አ በ2015 የኤፍኤ የሴቶች ዋንጫን ከአርሰናል ጋር ከዳሊያን ጋር ሁለት የሊግ ሻምፒዮናዎች እና በ2020 እንደዚሁ ኮፓ ዴ ላ ሬንና ሱፐርኮፓ አሁን ላይ ከምትገኝበት ከስፔኑ እግር ኳስ ክለብ ባርሴሎና ጋር ማሳከት ችላለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2019 የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ጎል ያስቆጠረች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ ተጫዋች ኦሾላ ፍጻሜውንም በማሸነፍ የመጀመሪያዋ ተጨዋች ናት። እ.ኤ.አ በ2024 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ሶስት ጊዜ በማሸነፍ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ ተጫዋችም ሆናለች።
በእርግጥ ዛሬ ላይ የተጫዋቿ ስኬት ከዚህም በላይ ሊዘረዘር የሚችል ይሁን እንጂ የመጣችበት የህይወት መንገድ በመግቢያችን አንደጠቀስነው አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ከቤተሰቦቿ አንስቶ እግር ኳስ እንዳትጫወት ጫና ይደረግባት እንደበር የምትገልጸው አሲሳት ኦሾላ አባቷ የእግር ኳስ ተጫዋች እንድትሆን እንደማይፈልግ ተናግራ በናይጄሪያ ጎዳና ላይ ከጓደኞቿ ጋር ስትጫወት ይወቅሷት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ “ወላጆቼ በጭራሽ ስፖርት እንድጫወት አይፈለጉም እና አንዳንድ ጊዜ በቤት ውስጥ ትልቅ ግጭቶች ነበር፡፡ ከችግር ለመዳን ወደ አያቴ ቤት ሸሽቼ እሄድ ነበር” ስትልም ተደምጣለች፡፡
እስካሁን በቃኘነው የእንስቶቹ የህይወት ጉዞ የምንረዳው ቁምነገር የቤተሰብ ድጋፍ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነና በተለይም ሴቶች ከልጅነታቸው ጀምሮ እንደ ዝንባሌያቸው ድጋፍ ከተደረገላቸው ውጤታማ እንደሚሆኑ ነው፡፡ በሀገራችንም ተሰጥኦ ኖሯቸው ከቤተሰብ በቂ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ከመንገድ የቀሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህንን ዕድል ያላገኙ ወጣቶች እንደዚህ አይነት ዕድል ቢመቻችላቸው ምን መስራት እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ስለ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ፈተናና መሰል ጉዳዮች በዳሰስንበት ጽሑፍ ያነጋገርናቸው የመጀመሪያዋ የወንድ እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ መሰረት ማኔ የሴቶች እግር ኳስ ቀስ በቀስ መሻሻሎች ቢኖሩትም ውጤታማ ለመሆን አሁንም ብዙ ይቀራል ብለዋል፡፡
አሰልጣኝ መሰረት ማኔ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት፣ ከመጫወቻ ሜዳ ጥራት ችግር አንስቶ፣ ትራንስፖርት፣ የላብ መተኪያ እና ሌሎች መሰረታዊ ነገሮች ሳይሟሉ ይጫወታሉ፡፡ የሴቶች ስፖርታዊ ተሳትፎ ከዚህ የበለጠ እንዲያድግ ሴት አሰልጣኞች፣ ዳኞች እና ሌሎች እግር ኳሱ የሚጠይቃቸው ባለሙያዎች መጨመር አለበትም የሚለውም ሀሳብ የአሰልጣኝ መሰረት ማኔ አስተያየት ነው፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ