የከተማ ልማት ሴፍቲኔት ፕሮግራሞች አፈጻጸማቸዉ አመርቂ ነው፡- የዓለም ባንክ

AMN- ህዳር 6/2017 ዓ.ም

በዓለም ባንክ በኩል ድጋፍ የሚደረግለት የከተማ ልማት ሴፍቲኔት ፕሮግራሞች አፈጻጸማቸዉ አመርቂ መሆኑን በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ፣ ኤርትራ ፣ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ማርያም ሰሊ ገለጹ ።

ዳይሬክተሯ በአዲስ አበባ የሚገኙ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል ።

ዳይሬክተሯ በተለይ የነገ ሃገር ተረካቢ ዜጎችን ማእከል ያደረገዉ የተማሪዎች ምገባ ፕሮጀክትንም አድንቀዋል ።

ለወጣቶችና ሴቶች የተፈጠሩ የስራ እድሎችና የስራ ክህሎት ማዳበሪያ ፕሮግራሞችም የሚደነቁ ናቸዉ ብለዋል ።

እነዚህ በተጨባጭ መሬት ላይ የወረዱ ፕሮጀክቶችንም የበለጠ ለማስፋፋት ባንኩ ድጋፉን ያጠናክራል ሲሉም ቃል ገብተዋል ።

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተገነባዉን የአቃቂ የመንግስት ትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ ማእከልን ጨምሮ ብቃት ፣ዛሬ ለነገ የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ ማእከሎች፣ የከተማ አስተዳደሩ ፕሮጀክት የሆነዉን የነገዋ የሴቶች ተሀድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማእከል ከተጎበኙት መካከል ናቸዉ ።

የገንዘብ ሚኒስተር ዲኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ፣ በምከትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ የስራ እና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ሚጀናን ጨምሮ ሌሎች የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተወካዮች በጉብኝቱ ላይ ተገኝተዋል ።

በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ የስራ እና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ 2016 እስከ 2020 ባሉት የመጀመሪያዉ ዙር የከተማ ልማት ሴፍትኔት ፕሮጀክቶች ከ400 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹን ለደገፈዉ የዓለም ባንክም ምስጋናቸዉን አቅርበዋል።

በሁለተኛዉ ዙር ፕሮጀክትም የከተማ ድህነት ቅነሳ እና የስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረቱን ማድረጉን ጠቁመዋል ።

በዚህም ከ 223 በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሲሆኑ ከዚህ ውስጥ 61 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸዉ ብለዋል ።

የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና በበኩላቸዉ የዓለም ባንክ እና የኢትዮጵያ መንግስት በከተማችን እና በክፍለ ከተማችን ባካሄዱት የሴፍቲኔት ስራዎች በነዋሪዎቻችን ህይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።

በዚህ ፕሮጀክት ከ8 ሺ 318 በላይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ግለሰቦች በሕዝብ ተሳትፎ ሥራ ተግባራት እንደተሳተፉ እና ከ4 ሺ 900 በላይ የሚሆኑት ተጠቃሚዎች ደግሞ ቋሚ እና ቀጥተኛ ድጋፍ እንዳገኙ ገልጸዋል ።

ይህ ፕሮጀክት በክፍለ ከተማው የሚኖሩ ከ11 ሺ 686 በላይ ነዋሪዎች ህይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳደረ መሆኑንም ጠቁመዋል ።

በአለማየሁ አዲሴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review