
AMN- ጥር 15/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የአገልጋይ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ቢሮ ሀላፊዋ በቃለ መጠይቃቸው አዲስ አበባ የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫና የሀገሪቱ መዲና እንደመሆኗ አስተማማኝ ሰላም መፍጠር ልዩ ትኩረት የሚፈልግ ተግባር በመሆኑ የተለያ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል ፡፡
ቢሮው ከለውጡ በኋላ የተቋቋመ ተቋም እንደመሆኑ 5 አመት ማስቆጠሩን ያስታወሱት ቢሮ ሀላፊዋ ወደ 22 ተግባራት በአዋጅ ተሰጥተውት እየሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል ፡፡
በተለይም ማህበረሰብን ባሳተፈ መልኩ የከተማዋንና የነዋሪዎችን ሰላም ፣ ፀጥታና ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኑ አብራርተዋል ፡፡
ባለፉት ጊዜያት እጅግ ውጤታማ ተልእኮዎችን ማከናወን የተቻለውም ለፀጥታ ስራው በተሰጠ ትኩረት መሆኑን ወ/ሮ ሊዲያ አስታውሰዋል ፡፡
ከተማው ላይ ያሉ የደህንነት ስጋቶችንና የወንጀል ምጣኔን በመቀነስ እንዲሁም ህገወጥነትን በመቆጣጠር ረገድ የከተማዋ ነዋሪ ከሚፈጠሩ የፀጥታ አደረጃጀቶች ጋር በመተባበር በተሰራው ስራ ውጤት ሊመዘገብ ችሏል ብለዋል ፡፡
መላው የከተማዋ ነዋሪ በህግና በደንብ ከተቋቋመው የሰላም ሰራዊት ጋር በመሆን ወንጀል በመከላከልና ወንጀለኛ ሲገኝ በመከላከል ረገድ ጠንካራ ስራዎችን ሰርተዋልም ብለዋል ቢሮ ሀላፊዋ ፡፡
በየሳምንቱ ሀሙስ ነዋሪው በየአካባቢው ሰላምና ፀጥታ ዙሪያ እንደሚመክር ያመለከቱት ወ/ሮ ሊዲያ የግለሰብ ግጭቶች ሲፈጠሩም ችግሩን በውይይት በመፍታት እርቅ የሚፈፀምበት አሰራር መዘርጋቱንም ጠቁመዋል ፡፡
በሽመልስ ታደሰ