የክልሉ እምቅ ፀጋ ለኢትዮጵያ ዕድገትና ብልጽግና ትልቅ አቅም ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

You are currently viewing የክልሉ እምቅ ፀጋ ለኢትዮጵያ ዕድገትና ብልጽግና ትልቅ አቅም ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

AMN – መጋቢት 13/2017

የአፋር ክልል ያለው እምቅ ሀብት እና ፀጋ ኢትዮጵያ ለመበልጸግ የያዘችውን ውጥን ለማሳካት የሚያስችል ሰፊ አቅም እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአፋር ክልል ጉብኝታቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በክልሉ በእንሳሰት መኖ፣ ስንዴ፣ ኢንዱስትሪ እና በኮሪደር ልማት እየተከናወኑ ያሉ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች እጅጉን ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በክልሉ ገጠሩን ከከተማው የሚያስተሳስር የልማት እሳቤዎችን በማሳናሰል የሚታሰበውን ብልጽግና የሚያስጨብጥ ጅማሮ እንዳለ ለመመመልከት መቻላቸውን ተናግረዋል።

በመስኖ እርሻ በ500 ሄክታር ገደማ የታረሰው አዲሱ የሳር ዝርያ አማካኝነት እየቀረበ ያለው የእንስሳት መኖ የዝናብ በድርቅ ምክንያት የቁም እንስሳቶች እንዳይጎዱ አስተዋጽኦ የሚያደርግ አዲስ ኢኒሼቲቭ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች እንዲሁ በቦረና እንስሳት በቂ መኖ እንዲያገኙ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ማስፋት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በአፋር ክልል ባለው ሙቀት ከዚህ ቀደም ስንዴ ማምራት የማይታሰብ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ሰዓት በበጋ መስኖ ከ1 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት ስንዴ እየተመረተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቀዳማዊ እመቤት ፅህፈት ቤት ተገንብቶ በሰመራ ከተማ በዕለቱ የተመረቀው የዳቦ ፋብሪካ በቀን 300 ሺህ ዳቦ እና 450 ኩንታል ዱቄት የማምረት አቅም እንዳለው ገልጸው ይህም የከተማዋን ነዋሪ ፍላጎት በበቂ ሁኔታ የሚያሟላ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል በአፋር ክልል ያለው የኮሪደር ልማት መልካም ጅማሮ እንደሚገኝ ጠቅሰው የመንገድ የፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓት መገንባት የመብራት ስርዓት መዘርጋት፣ የአረንጓዴ ልማት ስራ እና የከተማን ደረጃ የመጠበቅ ስራ በዋናነት በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የኮሪደር ልማት ስራው እስከ ቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ባለው ጊዜ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ጠቁመዋል።

በአፋር ክልል ያለው የእርሻ እና ኢንዱስትሪ ስራው አመርቂ የሚባል መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሁንና ክልሉ ካለው ሀብት እና ፀጋ አንጻር ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።

የክልሉን ሀብት በሚገባ መጠቀም ከተቻለ ለኢትዮጵያ ዕድገት እና ብልጽግና የሚጠቅም ትልቅ አቅም እንዳለው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በሀገሪቷ ያሉትን ሀብቶች አይንን ገልጦ በመመልከት እና በትጋት በመስራት መጠቀም እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review