የኮሪደር ልማቱ ለዜጎች ምቹ አካባቢን ከመፍጠር ባለፈ ለከተማው እድገት የላቀ ሚና እያበረከተ ነው-ኢንጅነር አይሻ መሀመድ

AMN – ታኅሣሥ 2/2017 ዓ.ም

የኮሪደር ልማቱ ለዜጎች ምቹ አካባቢን ከመፍጠር ባለፈ ለሀረር ከተማ እድገት የላቀ ሚና እያበረከተ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለፁ።

የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በሀረር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ሚኒስትሯ በመስክ ምልከታው እንደገለፁት የኮሪደር ልማቱ ለዜጎች ምቹ አካባቢን ከመፍጠር ባለፈ ለሀረር ከተማ እድገት የላቀ ሚና እያበረከተ ይገኛል።

የኮሪደር ልማት ስራው በሀረር ከተማ እየታየ ለሚገኘው ተጨባጭ ለውጥ አንዱ ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።

በኮሪደር ልማቱ እየተከናወኑ የሚገኙ የመኪና፤ የእግረኛና የሳይክል መንገዶች እንዲሁም የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ከተማውን ውብ ገፅታ በማላበስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ መልኩ አለም አቀፍ ቅርስ በሆነው ጁገል ውስጥና ዙሪያ እየተሰሩ የሚገኙ የመልሶ ልማት ስራዎች ቅርሱን ተንከባክቦ ከማቆየት ባለፈ ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆን እያስቻለና ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በኮሪደር ልማቱ ሀረርን በምሳሌነት የምትጠቀስ ከተማ ለማድረግ እየተደረጉ የሚገኙ ርብርቦችን ማስቀጠል እንደሚገባም ኢንጅነር አይሻ መሀመድ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በጉብኝቱ ላይ ሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድ፣ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ፣ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሮዛ ኡመርን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review