የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባ በተሟላ የከተሜነት ፅንሰ ሃሳብ እንድትመራ አድርጓታል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባ በተሟላ የከተሜነት ፅንሰ ሃሳብ እንድትመራ አድርጓታል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- የካቲት 12/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት እያካሄደ ባለው የ2017 ዓ.ም 4ኛ የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤው ላይ ተገኝተው የ6 ወራት የሥራ አፈፃፀም ያቀረቡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባ በተሟላ የከተሜነት ፅንሰ ሀሳብ እና የመሠረተ ልማት ሥርዓት እንድትመራ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ 3ሺ 515 ሄክታር ቦታን የሚሸፍን ሲሆን 136 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአስፋልት መንገድ ግንባታን የሚያጠቃልል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

አክለውም 246 ኪ.ሜ የእግረኛ መንገድ፣ 431 ሄክታር የአረንጓዴ ቦታዎች ግንባታ፣ 141 ኪ.ሜ የብስክሌት መንገድ፣ 53 የህፃናት መጫወቻዎች፣25 የታክሲና አውቶቢስ መጫኛና ማውረጃ፣ 8ዐ የመኪና ማቆሚያዎች እና 23 የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን ያካትታልም ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም 112 የህዝብ መጸዳጃ ቦታዎች፣ 92 ኪ.ሜ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች፣ ደረጃውን የጠበቀ የከተማ መብራት፣ የቴሌኮም መሰረተ ልማት 266 ኪ.ሜ፣ የደህንነት መጠበቂያ ቴክኖሎጂዎች ዝርጋታ 197 ፋየር ሀይድራንት እንዲሁም 1ሺ 969 ህንፃዎችን እድሳት በማካተት በግንባታ ላይ ሲሆን በተያዘለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅም አስታውቀዋል፡፡

2ኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ ከመጀመሪያው የኮሪደር ልማት ሥራ ልምድ በመቀመር በፍጥነትና በጥራት 24/7 እየተተገበረ እንደሚገኝ ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተናገሩት፡፡

ይህ የኮሪደር ልማት ሥራ ከተነሽዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶችን በመፍጠር እንዲሁም ክፍተቶችና ቅሬታዎች ሲገጥሙ በገለልተኛነት መፍትሄ የሚሰጥ አደረጃጀት በመዘርጋት የተመራ ነው ብለዋል፡፡

በመልሶ ማልማቱ ለተነሱ ነዋሪዎች ወደ 9 ሺ የሚደርሱ የመኖሪያ ቤቶች፣ 1ሺ 402 የመስሪያ ሼዶች፣ 200 የንግድ ሱቆች፣ 2ሺ 124 የመስሪያ ቦታዎች እና ወደ 3000 ለሚደርሱት ደግሞ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ቋሚ የሥራ እድል እንዲያገኙ መደረጉን በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡

በኮሪደር ልማቱ ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን መደረጉን የተናገሩት ከንቲባ አዳነች የአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ መሻሻል፣ የተወዳዳሪነት አቅም መፈጠሩ፣ የሥራ ባህል መሻሻል (24/7) የታየበት፣ የፕሮጀክት አመራርና የኮንትራት አስተዳደር አቅም ያሳደግንበት እና ሌሎችም በርካታ ውጤቶች ያገኘንበት ነው ብለዋል፡፡

ለተገኘው ውጤት በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አዲስ አባባ እንደ ስሟ ውብ፣ አበባና፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ እንድትሆን ሌት ተቀን እየሰጡት ላለው አመራር፣ ክትትልና ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሂደቱ ትልቅ ሚና እየተወጡ የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች እና ተቋማትንም ከንቲባ አዳነች አመስግነዋል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review