AMN – የካቲት 18/2017 ዓ.ም
ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቀበታ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ባሕር ዳር በተፈጥሮ የተዋበች ከተማ ናት ብለዋል። በከተማዋ እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት ተጨማሪ ውበት እየኾናት መኾኑን ገልጸዋል። የኮሪደር ልማቱ ከጣና ሐይቅ ጋር ተያይዞ የሚሠራ በመኾኑ የተለየ ውበትን የሚያላብስ ነው ብለዋል።
የጣና ሐይቅ ለባሕር ዳር የቱሪዝም ሃብት መኾኑንም ገልጸዋል። የኮሪደር ልማቱ የጣና ውበትን የገለጠ፣ የከተማዋንም ተፈላጊነት የጨመረ ነው ብለዋል። የኮሪደር ልማቱን እየመሩ ያሉ መሪዎች እውቅና ሊሰጣቸው እንደሚገባም ተናግረዋል። ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ስታዲዬም ግንባታም ለከተማዋ ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ እንደሚኾንም ተናግረዋል። የስታዲዬሙ ግንባታ ጎብኝዎች ወደ ከተማዋ እንዲመጡ ያደርጋል ነው ያሉት።

ዘላቂ የኾነ የሀገር ልማት ለማረጋገጥ ዘላቂ እና አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሯ ለዚህ ደግሞ የሀገር ውስጥ ገቢን መሰብሰብ ይጠበቃል ብለዋል። በብድር ያደገ ሀገር አለመኖሩንም ተናግረዋል። የአማራ ክልል ልማት እንዲያድግ፣ ጤናማ የፋይናንስ ስ
ሥርዓት እንዲኖር የገቢ አሰባሰብን ማሳደግ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ክልሉ ያለውን ትልቅ አቅም መጠቀም ያስፈልጋልም ብለዋል። በአማራ ክልል ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን መገንዘባቸውን ተናግረዋል። ክልሉ ያለውን በቂ ሃብት በመጠቀም መበልጸግ ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ ከተጠቀምንበት ይልቅ ያልተጠቀምንበት ይበልጣል ነው ያሉት። ክልሉን ወደ ኋላ ከሚጎትቱ አካሄዶች መጠበቅ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቀበታ በባሕር ዳር ከተማ እየተሠራ ያለው ልማት የሚደንቅ መኾኑን ገልጸዋል። የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ውበት የጨመረ ነው ብለዋል። የባሕር ዳር ስታዲዬም በሀገር ውስጥ እንዲኖር ስንመኘው የነበረ ዓይነት ስታዲዬም ነው ብለዋል። የሚያኮራ እና የሚያስደስት መኾኑንም መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ከክልሉ ውጭ ሲኖሩ ጦርነት እና ግጭት ብቻ ነው የሚሰማው ያሉት ኮሚሽነሩ በአካል ስንመለከተው ግን የጸጥታ ችግር የነበረበት አካባቢም አይመስልም ነው ያሉት።