የወንዝ ዳርቻዎችን ከማልማት ባሻገር

You are currently viewing የወንዝ ዳርቻዎችን ከማልማት ባሻገር

ደንቡ ጤናማ የሆነ የወንዝ ዳርቻ ልማት እንዲኖር አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑ ተጠቁሟል

በሀገራችን ያሉ ወንዞች አፍ ኖሯቸው ቢናገሩ ምን የሚሉ ይመስላችኋል? አንዳዶች “በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል“ ከሚለው ብሂል አላቅቃችሁናል፣ ሌሎች ደግሞ “የበይ ተመልካች“ከመሆን ወጥታችኋል የሚሉ ይመስለኛል፡፡ ጥበብ ደግሞ ቁጭት በመፍጠር በጎ ስራ እንድንሰራ በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋኦ አድርገዋልማለት ይችላል፤ከሚፈለገው አንጻር በቂ ባይሆንም፡፡

የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና

የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የፀና

ከጥንት ከፅንሰ አዳም ገና ከፍጥረት

የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከገነት

ግርማ ሞገስ

ያገር ፀጋ ያገር ልብስ

ዓባይ

የበረሀው ሲሳይ… ስትል እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ስለ ዓባይ በአይረሴ ስንኝ እና በጆሮ

ገብ ዜማ ዘመን ተሻጋሪ ስራ አበርክታልናለች፡፡ ዓባይ የበረሃ ብቻም ሳይሆን የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት (ግብፅ እና ሱዳን) ሲሳይ ሆኖም ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያውያን በቁጭት ከጫፍ ጫፍ ተነስተው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመገንባት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ማድረስ ችለዋል፡፡ ኤሌክትሪክ ሀይልን ጨምሮ መሰል ትሩፋቱንም መቋደስ ጀምረዋል፡፡ ግድቡ ረጅም እድሜ እንዲኖረው ጥራት ባለው መልኩ መስራት እንደተጠበቀ ሆኖ ደለልን ለመከላከል የአረንጓዴ ልማቱ አካል ተድርጎ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡

ይህን ጉዳይ እንደመግቢያ ያነሳሁት የአዲስ አበባ ወንዞችም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር ስላላቸው ነው፡፡ የከተማዋ ወንዞች ድምጻዊ ፀሐዬ ዮሐንስ ቀበናን በተመለከተ፡-

… በጋ ሆነ ክረምት በፀሐይ ደመና

ከዚህ ከዚያም መጥተን ዋኝተናል

ቀበና

ምንም ብንራራቅ ቢለያይ ደብራችን

ከማዶ እስከ ማዶ አንድ ነው ወንዛችን

በዘመን ኮርቻ ቢገሰግስ ጊዜ

የልጅነት ሳቄን አስታወሰኝ ወንዜ… ሲል ባዜመበት መንገድ የሚገለጹ ናቸው፡፡ ወንዞቹ መሰባሰቢያ፣ ጽዳትም፣ ጉርስም፣ የመዝናኛ አማራጭም ሆነው ቆይተዋል። ሆኖም ወንዞቹን ማልማት ብሎም በአግባቡ መጠበቅ ላይ የተፈጠረው መዘናጋት ወዛቸው እንዲወይብ፣ በጉጉት አፍ የሚያስከፍቱ ሳይሆን በመጥፎ ሽታ አፍንጫን የሚያስይዙ እንዲሆኑ አድርጓቸው ቆይቷል፡፡ የሞቱ እንስሳትን ጨምሮ ቆሻሻን በግዴለሽነት መጣላቸው፣ የቤት ውስጥ ፍሳሽ ከወንዞች ጋር መገናኘታቸው፣ ድርጅቶችን ጨምሮ ተቋማት ተረፈ ምርቶቻቸውንና በካይ ኬሚካሎቻቸውን መልቀቃቸው እና መሰል ህገ ወጥ ተግባራት ለዚህ በማሳያነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የአስተያየት ሰጪዎች ትዝብትም ከዚህ እውነት የወጣ አይደለም፡፡ የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ ከዚህ በፊት የነበረው የወንዝና የወንዝ ዳርቻዎች አያያዝ፣ እንክብካቤ፣ ልማት የዘፈቀደ ነው፤ በህግ እና በመመሪያ የሚመራ አይመስልም ነበር፡፡ አካባቢዎቹ ለመኖሪያም፣ ለመዝናኛም ምቹ አልነበሩም፡፡ አደገኛው አስተሳሰብ ደግሞ አዲስ አበባን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ከተሞች የመኖሪያ ቤትን የፍሳሽ መስመር ወንዞች ጋር የማገናኘት ሁኔታ መስተዋሉ ነው፡፡ በጥቅሉ ወንዞቹን ለኑሮም፣ ለመዝናኛም በሚመች መልኩ የማልማቱ ጉዳይ የተተወ ጉዳይ ሆኖ እንደቆየ አብራርተዋል፡፡

ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ቁስቋም መቀጠያ በሚባለው አካባቢ እንዳደጉ እና አሁንም እየኖሩ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ያለለት አስናቀው በበኩላቸው፣ “በተለምዶ ማሪያም ተብሎ በሚጠራው ወንዝ ልብስ እናጥብ፤ ሻወር እንወስድ ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወንዙ አይደለም ለሻወር እና ለልብስ ማጠቢያ ሊሆን ቀርቶ ለማየት የሚያስጠላ፣ ሽታው የከፋ፣ እንስሳት የሚያረቡ ሰዎች ከዚህ ጋር አገናኝተው ጽዳጃቸውን የሚለቅቁበት ሁኔታ ይስተዋላል፤ በዚህም ውሃው ወደ ጥቁርነት እስከመቀየር ደርሶ ነበር” ብለዋል፡፡

ልክ ዓባይን ከበረሃ ሲሳይነት ለኢትዮጵያ በረከት ወደሚሆንበት መንገድ እንደቀየርነው ሁሉ በመዲናዋ የሚገኙ ወንዞችን ወደ ቀደመ ወዛቸው እንዲመላለሱ በማድረግ ረገድ አበረታች ስራ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከፍተኛ አመራሩ ድጋፍና ክትትል ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ከሰሞኑ እንኳን ሁለተኛው የኮሪደር ልማት ስራ የደረሰበት ደረጃ በከፍተኛ አመራሩ ሲገመገም የወንዝ ዳርቻ ልማቱ የዚያ አካል ነበር፡፡ ልማቱ የወንዞችን የቀደመ ህመም ከማከም አንጻር ስለሚያበረክተው አስተዋጽኦ አቶ ጥጋቡ ሲያብራሩ፣ “ጤናማ ለሆነ የሰዎች እንቅስቃሴ፣ ጽዱ እና አረንጓዴ አካባቢን ከመፍጠር፣ የመዝናኛ አማራጮችን ከማመቻቸት በተጨማሪ ለዓይንም ሳቢና ማራኪ እንዲሆኑ አብዮት ፈጥሯል። ከፍተኛ የሆነ ልዩነት አምጥቷል፡፡ አሁን ላይ የወንዝ እና ወንዝ ዳርቻዎች በትክክል ለሰው ልጆች ኑሮ፣ እንቅስቃሴ፣ መዝናኛ እና ማህበራዊ አገልግሎት እንዲውሉ ትልቅ ዕድል የፈጠረ ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ልማቱ ያመጣውን ትሩፋት በአግባቡ ማጣጣም፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የልማቱን ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ተግባራዊ ማድረግ ብልህነት ነው፡፡ ለዚህ ይመስላል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ ቁጥር 180/2017ን አውጥቶ ተግባራዊ በማድረግ ላይ የሚገኘው፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በተለይ ከለውጡ ወዲህ ጥሩ እና ተራማጅ ህግና ደንቦችን አውጥቷል፡፡ ከእነዚህ መካከል ወንዝና ወንዝ ዳርቻዎችን የተመለከተው አንዱ ነው የሚሉት የህግ ባለሙያው፣ ህገ ወጥነትን ለመከላከልና ጤናማ የሆነ የወንዝ ዳርቻ ልማት እንዲፈጠር አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ሰዎች በምቹና ጤናማ አካባቢ እንድንኖር የህገ መንግስቱ ድንጋጌም ጭምር ነው፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 44 ላይ ሰዎች በንጹህና ጤናማ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው ይላልና” የሚሉት ባለሙያው፣ በንጹህና ጤናማ አካባቢ የምንኖረው የጸዳ ቤት ስላለ፣ የጸዳ መንገድ ስለተገነባ፣ አጠቃላይ የምንጠቀምባቸውን ነገሮች ንጽህ፣ ጽዱ፣ ማራኪና ምቹ በማድረግ ብቻ አይደለም። እንደ ወንዝ ዳርቻ አይነት ተጓዳኝ የሆኑ የአካባቢ ልማቶችን ታሳቢ ማድረግ ሲቻል ጭምር ነው፡፡ ልማቱን ቀጣይነት፣ ህጋዊነት እና ተገቢ ካልሆነ አያያዝ ከምንጠብቅባቸው መንገዶች መካከል አንዱ ደንብ ወይም የህግ ማዕቀፍ ነው። ይህ ደንብ መውጣቱ ደግሞ ወቅታዊ እና ተገቢነት ያለው ነው፡፡ ለወንዞች አጠቃላይ ልማት ዕድል የሚፈጥር ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

የወንዝ ዳርቻ ልማት ሳቢ፣ ማራኪ፣ ለከተማ ነዋሪ ምቹ በማድረግ እና በማስተዳደር በኩል ብዙ ሀገራት የተሻለ ልምድ እና ተሞክሮ አላቸው፡፡ ለምሳሌ፡-

የማሌዢያ ከተሞች፣ ሲንጋፖር፣ ከደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ያሉ ከተሞች በተሻለ የወንዝ ዳርቻ ልማት እና ጥበቃ ይጠቀሳሉ፡፡ ለሀገራቱ ከተሞች ውጤታማነት ህግ ማውጣታቸው አንዱ ሆኖ ተጠያቂ የማድረግ አቅማቸውም ከፍ ያለ መሆኑ፣ ህጉ በአግባቡ እንዲተገበር የክትትልና ቁጥጥር ስራ መስራታቸው፤ ህብረተሰቡ ላይ የባለቤትነት ስሜት በማስረጽ ከተቋማት ጎን ማሰለፋቸው ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡

እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ የወንዝና ወንዝ ዳርቻዎችን በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል ብሎም ለከተማዋ ነዎሪዎች ምቹና ማራኪ ለማድረግ ሁለት ነገር ይጠበቃል፡፡ አንደኛው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ላይ ሚዲያዎችን ጨምሮ በሚመለከታቸው ተቋማት በመስራት ህዝብን ማንቃትና ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራርን ይፈልጋል፡፡ ሁሉም ሰው ያልተገባ ነገር ሲጣል፣ ሲፈጸም ካዬ “ለምን?” ብሎ የመጠየቅ፣ የመቆርቆር፣ አጥፊዎችንም ለህግ አካላት አሳልፎ የመስጠት ኃላፊነት አለበት፡፡   

የአዲስ አበባ ከተማ የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ጉዳዩን አስመልክቶ ከሰሞኑ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሰጡት ማብራሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራው በሁለት መልኩ እየተሰራ መሆኑን፣ “የባለስልጣኑ ሰራተኞች የወንዞችን የብክለት መጠን በሚገባ እንዲረዱ እንዲሁም ስለደንቡ የተሟላ እውቀት እንዲኖራቸው ስልጠና የመስጠት ስራ በአንድ በኩል ተከናውኗል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለወንዝ ዳርቻ ብክለት መነሻ ናቸው የሚባሉ መንግስታዊ እና የግል ተቋማት፣ ጋራዦች እና ሌሎችም እንዲሁም በወንዝ ዳርቻ አካባቢ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በጥናት የመለየት ስራ ከተሰራ በኋላ እነዚህን አካላት ታሳቢ ባደረገ መልኩ በከተማ ደረጃ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ተሰርተናል። ይህ ግንዛቤ ፈጠራ ከክፍለ ከተማና ወረዳ እስከ ብሎክ ድረስ የማዳረስ ስራ እየተከናወነ ነው” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በወንዝ ዳርቻዎች አካባቢ ቆሻሻ እንዳይጣሉ ከመቆጣጠር አንጻር አሁን ላይ በቂ የሰው ኃይል እንዳላቸው የገለጹት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ በቀጣይ ስራውን በቴክኖሎጅ የማስደገፍ ሀሳብ መኖሩንና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ጋር በመሆን እንደሚሰራ አክለዋል፡፡

ወንዞችን ከብክለት መታደግ ለከተማዋ ጽዳት እና ለነዋሪዎቹ ምቹ ከባቢን ከመፍጠር አንጻር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው፡፡ ደንቡ የመውጣቱ ምስጢርም በዚህ ላይ ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ ውጤት ለማምጣት ነው፡፡ ስለዚህ ለሆነ አካል ሳንተወው ሁላችንም የድርሻችን ኃላፊነት እንወጣ መልዕክታችን ነው፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review