AMN- ጥር 19 /2017 ዓ.ም
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኢኖንሴባ ሎሲን በዛሬው ዕለት በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይታቸውም በሁለትዮሽና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን የሁለቱን ሀገራት የቆየና ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
ዶ/ር ጌዲዮን፣ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሃገራት መሆናቸውን ጠቅሰው ፤ አፍሪካ ኀብረትን ጨምሮ በበርካታ ባለብዙ መድረኮች ላይም በትብብር እንደሚሰሩ ገልፀዋል ።
የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኢኖንሴባ ሎሲ በበኩላቸው፣ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሠሩ ገልፀው ፤ ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር በአፍሪካ ህብረት፣ በብሪክስ ማዕቀፍ እንዲሁም በሌሎች ዓለም ዓቀፍ መድረኮች የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል ።
አምባሳደሯ በመጭው ወር ለሚካሄደው ለ38ተኛ የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባኤ ስኬትም በትብብር እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።