AMN – የካቲት 9/2017 ዓ.ም
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ከማዳጋስካር አቻቸውራሳታ ራፋራቫቪታፊካ ጋር ተወያይተዋል።
ሚኒስትሮቹ በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊ እና በዓለም አቀፋዊ የጋራ ፍላጎቶች ዙሪያ ያለውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ውይይት አድርገዋል።
የአጃንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት በንግድ፣ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንት፣ በአካባቢ ሥነ ምህዳር ጥበቃ፣ በዕደ ጥበብ እና በቅርስ ጥበቃ ዙሪያ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል።

ኢትዮጵያ እና ማዳጋስካር የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ እና የፖለቲካ ምክክር በማድረግ የትብብር መስኮቻቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም ገልፀዋል።
የማዳጋስካር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራሳታ ራፋራቫቪታፊካ በበኩላቸው፥ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
በቅርስ አጠባበቅ፣ በአቪዬሽን፣ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የልምድ ልውውጥ ለማድረግም ዝግጁ መሆኗን መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።