
AMN-ኅዳር 19/2017 ዓ.ም
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ከእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዝዳንት ጂን ሊኩን ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ውይይታቸው በኢትዮጵያ እና በባንኩ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር በሚያስችሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተመልክቷል፡፡
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እየተገበረች ስላለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፎች እየተሰሩ ስለሚገኙ ስራዎች ለባንኩ ፕሬዝዳንት ገለፃ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በያዘችው የልማት ፕሮግራም የምትገነባቸው ግዙፍ የመሠረተ ልማት አውታር ፕሮጀክቶች ከሀገር ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር ያላቸው ሚና ቁልፍ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጨምረው ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ እና የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ መኖሩን በመጥቀስ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዝዳንት ጂን ሊኩን በበኩላቸው ኢትዮጵያ አምቅ የእድገት አቅም ያላት እና በኢኮኖሚ እድገት ላይ ያላች መሆኗን ገልጸዋል።
ባንኩ ቁልፍ የሆኑ የመሠረተ ልማት አውታሮችን በማስፋፋት ዙሪያ ከመንግሥት ጋር በቀጣይ አብሮ የመስራት ፍላጎት እንዳለው ፕሬዝዳንቱ መግለጻቸውም ተመላክቷል።
የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ እ.ኤ.አ በ2016 የተመሰረተ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ የአባል ሀገራቱ ቁጥር 110 መድረሱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።