የታሪክ ምሁራን “ሰውነት የከበረበት” ድል ነው ይሉታል፤ ዓድዋን፡፡ በርግጥም ዓለም ከዓድዋ ድል በፊት ሚዛኗ የተንሻፈፈ ነበር፡፡ ሰውን በቀለሙ የምትለይ፣ ለነጭ የምታደላ፣ ነጮች ጥቁሮችን በርሃብ አለንጋ የሚገርፉባት፣ የምንዱባን እምባ ያበቀለውን በጨካኞች ጅራፍ የተሰነጣጠቀ ጉልበት ያፈራውን ከቁምጣን በላይ የሚበሉባት፣ በሰዎች ክፋት የመረረች ምድር ሆና ነበር፡፡ ዓለም ብዙዎች ጥቁር በመሆናቸው ብቻ በባርነት ቀንበር እጅ ከወርች ታስረው አምርረው ያለቅሱባት ነበር። የዓድዋ ድል ግን ይህን ሁሉ ታሪክ ቀየረው፤ የዓለም ስርዓትን በአዲስ ቅኝት ውስጥ ያስጉዘውም ጀመር፡፡
አውሮፓውያን በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢንዱስትሪዎቻቸውን ባስፋፉ ማግስት ተንኮልን አብዝተው አሰቡ። ለኢንዱስትሪዎቻቸው ጥሬ ሀብት ለመቀራመት እና ለምርቶቻቸው ማራገፊያነት ትሆን ዘንድ አፍሪካን መረጡ፡፡ እ.ኤ.አ በ1884 እና በ1885 ዓ.ም አውሮፓውያን በጀርመን በርሊን ከተማ ተሰብስበው አፍሪካን ለመቀራመት ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ ስምምነቱም “የበርሊን ስምምነት” በመባል ይታወቃል። ስምምነቱን ተከትሎ የወቅቱ የአውሮፓ ኃያላን ሀገራት አፍሪካን መቀራመት ጀመሩ። አፍሪካን እንደ ቅርጫ ስጋ ተከፋፈሏት፡፡ ጥቁሮችም በአህጉራቸው የባርነትን ቀንበር ተሸክመው በመላው ዓለም የመከራ ዶፍ ዘነበባቸው፡፡
በዚያ ክፉ ዘመን ሚዛኗ በተንሻፈፈው ዓለም ሕይወት ለጥቁሮች ትርጉም አልባ ነበረች፡፡ ጥቁሮች ተስፋቸው በድቅድቅ ጨለማ በጥቁር ድንጋይ ላይ እንደሚንቀሳቀስ ጉንዳን የማይታይ ሆነ፡፡ ከሰማይ በታች ይመኩበት ጦር፤ ይጠለሉበት ዋሻና ጋሻ አጥተው እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው፡፡
ገጣሚና ባለቅኔ ደበበ ሰይፉ የብርሃን ፍቅር በተሰኘው መድብሉ “ብቻ መገኘትሽ” ሲል በከሸናት ቅኒያዊ ግጥም –
…ታውሮ እንደኖረ እንደ አንድ ጎበዝ
በድንገት ብልጭታ እንዲደነዝዝ
በጨለማ ቤቴ አንቺ ጮራይቱ
ዘው በማለትሽ ቢጠፋኝ ብልሃቱ፣
እንባውም ይደርቃል
ብልሃቱም ይገኛል፤
የወጣሽው ፀሐይ ጽልመቱ ሲሸሽ
ብቻ መገኘትሽ
ብቻ መኖርሽ፡፡ እንዳለ- ለዓለም ጭቁን ህዝብ የነፃነት ብርሃንን ከጫፍ ጫፍ የምትፈነጥቀው ፀሐይ የዓድዋ ተራሮችን መሐል ለመሐል ሰንጥቃ ወጣች፡፡ እለተ ሰንበት በየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም የወጣችው ይህች ፀሐይ የብዙዎችን ፅልመት የገፈፈች፤ እብሪተኞችንም አንገት ያስደፋች ሆነች፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ኑሩ ይማም እንደሚሉት፣ ዓድዋ ትልቅ የጀብዱ ስራ የተሰራበት፣ ‘አይሸነፉም’ የተባሉት ነጮች በጥቁሮች የተሸነፉበት፣ የታሪክ ምዕራፍ የተቀየረበት፣ የጥቁር ህዝብ የአሸናፊነት ህያው ምስክር ነው። የዓድዋ ድል በወቅቱ የነበረውን የዓለም ስርዓት ቀይሯል፤ ነጮቹ ዓለም እንድትጓዝበት የቀየሱትን የበላይና የበታች ስልት ቀልብሷል፤ የዓለማችን የተሳሳተ ብይን ፉርሽ እንዲሆንም አድርጓል፡፡ ሰው በሰውነቱ የሚከበርበትን አዲስ ብርሃንም ፈንጥቋል፡፡
የታሪክ ምሁሩ ጆርጅ በርክለይ እ.ኤ.አ በ1902 በፃፉት “ዘ ካምፔይን ኦፍ ዓድዋ ኤንድ ዘ ራይዝ ኦፍ ምኒልክ” የተሰኘ መጽሐፋቸው የኢትዮጵያን ልዕልና ከአውሮፓ አንፃር እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል፤ “ሐበሾች ገናና ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል፡፡ የኛ ዓለም ገና ቶር እና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ ሐበሾች የክርስትናን ኃይማኖት የተቀበሉ ናቸው። ዛሬ ደግሞ የዓድዋ ድል አንዱን የበላይ ሌላውን የበታች የሚያደርገውን ሚዛን አስተካከለው፡፡ ስህተት የሆነውን የአውሮፓውያኑን ፍላጎት ዓድዋ ዘጋው”
ታዲያ ጆርጅ በርክለይ በዓድዋ ጦርነት ትረካቸው ለጣሊያን ግልፅ ወገናዊነታቸውን ቢያሳዩም የድሉን ግዝፈት ግን መካድ አልቻሉም ነበር። እናም ካለፈው የታሪክ ትንታኔ አኳያ የዓድዋ ጦርነት በአፍሪካ ምድር አዲስ ኃይል መነሳቱን ያሳያል ብለዋል፡፡ “የዚህች አህጉር ተወላጆች የማይናቅ ወታደራዊ ኃይል መሆን እንደሚችሉ ልናሰላስል ተገድደናል፡፡ እንዲያውም ነገሩ አስቂኝ ቢመስልም ይህ ሁኔታ ጨለማይቱ አህጉር አፍሪካ- በትከሻዋ ላይ ስልጣኑን ባንሰራፋው አውሮፓ ላይ የምታደርገው አመፅ የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው” ሲሉ ስለ ዓድዋ ድል ከፍታ መስክረዋል፡፡
የዓድዋ ድልን ተከትሎ ዓለም ያስተናገደቻቸውን ክስተቶችን አስመልክቶ የተለያዩ የታሪክ አጥኚዎች የተለያዩ ነጥቦችን አስፍረዋል። ለአብነትም ዓድዋ:- አፍሪካ ውስጥ አውሮፓውያንን የሚገዳደር ወታደራዊ ኃይል እንዳለ አሳይቷል። አፍሪካን ተቀራምተዋት በነበሩት ቅኝ ገዢዎች ላይ ስጋትን ፈጥሯል። ነጮች በጥቁሮች ላይ የነበራቸውን የኃያልነት ትርክት ከመሰረቱ ቀይሯል። ዓድዋ ኢትዮጵያ ለጥቁሮች የነጻነት ቀንዲል ሆና እንድትታይ አድርጓታል።
የዓድዋ ድል የጣሊያንን መስፋፋት ቀያሽ የነበረው የፍራንሲስኮ ክርስፒ አስተዳደር እንዲወድቅ ምክንያት ሆኗል። የዓድዋን ጦርነት የመራው ጀነራል ባራቲየሪ ውድቀት ሆኖ ለሽንፈቱ ክስ ተመስርቶበትም ነበር። በመጨረሻም የዓድዋ ጦርነት ምክንያት የነበረውን የውጫሌ ስምምነትን ውድቅ የሚያደርገውና የኢትዮጵያን ነጻ ሀገርነት የሚቀበለውን የአዲስ አበባ ስምምነት ጣሊያን እንድትፈርም አድርጓል። በርግጥም ዓድዋ ሀሰትን በእውነት፣ መድሎን በኩልነት፣ የአይቻልም መንፈስን በይቻላል የቀየረ ድል ነው ሲሉ የታሪክ ምሁራኑ መስክረዋል፡፡
የታሪክ መምህር ኑሩ እንደሚሉት፣ የዓድዋ ድል በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በቅኝ ግዛት አስተዳደር ስር ወድቀው በነበሩ የላቲንና የእስያ ሀገራት የነፃነት ተጋድሎ እንዲቀጣጠል ምክንያት ሆኗል። የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በዓድዋ ጦርነት ዓለም የተደመመበትና ዛሬም ድረስ እንቆቅልሽ የሆነበት ደማቅ ታሪክ በጀግኖች አባቶች ተሰራ። ከንጋቱ 11:00 ሰዓት ማርያም ሸዊቶ፣ በሶሎዳ፣ ረቢ አርእየኒ፣ አዲ ተቡን በሚባሉና በሌሎቹም የዓድዋ ተራሮች ላይ የመሸገው የኢትዮጵያ ጦርም መሃል የገባውን ጠላት እንደ በጋ ስንዴ እያጨደ መሬት ላይ እንዳሰጣው ታሪክ ምስክር ነው።
የጣሊያን መንግስት ለብዙ ጊዜ የተዘጋጀበት ጦርነት በአምስት ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ተደመደመ። ጀግኖች አባቶች ዓለምን ያስደመመ ደማቅ ድል በደምና አጥንታቸው ጻፉ። ድሉም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነፃነት ከማስከበር አልፎ ለመላው ጥቁር ህዝብና በቅኝ ግዛት ባርነት ውስጥ የነበሩ የእስያና ላቲን ሀገራት ለነፃነታቸው እንዲታገሉ ትልቅ የሞራል ስንቅ እንደሆነ የታሪክ መምህር ኑሩ ይናገራሉ።
መምህር ኑሩ ዓድዋ ዓለም አቀፋዊ ድል ሆኖ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴዎች ሁሉ መነሻ እስከመሆን መብቃቱን ይናገራሉ። ጃማይካዊውን ማርከስ ጋርቬይ ጨምሮ የነጻነት ታጋዮች ዓድዋን “የይቻላል መንፈስ ማጋቢያ” አድርገው በስፋት ተጠቅመውበታል፡፡ ትግላቸውንም አቀጣጥለውበታል።
አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት መላቀቅ ከጀመሩ በኋላ በአንድነት መቆም እንደሚገባቸው አምነው በ1963 ለአቋቋሙት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዓድዋ ድል መሰረት ተደርጎ ይወሰዳል። ከ10 በላይ የአፍሪካ ሀገራት ከነጻነት በኋላ የሰንደቅ ዓላማቸውን ቀለም ከኢትዮጵያው አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ጋር ማዋደዳቸው ዓድዋ የፈጠረው የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አካል ተደርጎ እንደሚወሰድም የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ።
ዓድዋ ጥበብ ነው፤ ዓድዋ ጀግንነት፤ ዓድዋ እውነት ነው ውሸት በአደባባይ የተረታችበት፡፡ ዓድዋ ቅርብ ነው ከመንፈሳችን የተዋደደ፣ የተዋሀደ፤ ዓድዋ እሩቅ ነው! ከምጥቀት በላይ ከጥልቀትም በታች እጅግ የረቀቀ፡፡
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን ወዝና ደርዝ ባለው ቅኔያዊ ግጥሙ
…ዓድዋ ሩቅዋ
የዓለት ምሰሶ የአድማስ ጥጓ
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳሷ … እንዳለው።
ስለ ዓድዋ ከተፃፉ መፅሐፍት መካከል የዓድዋ ጦርነት (THE BATTLE OF ADWA) የተሰኘው መፅሐፍ አንዱ ነው፡፡ በመፅሐፉ እንደተገለፀው፣ ኢትዮጵያ በአውሮፓ ኢምፔሪያሊዝም ላይ የተቀዳጀችው የዓድዋ ድል የሰው ልጆች ሁሉ እኩል መሆናቸውን በሚገባ ያረጋገጠ ዝንፍ የማይል መለኪያ ነው፡፡
ዓድዋ በዘመን ጅረት ሳያረጅ ሰርክ አዲስ እንደሆነ እና ሁሌም እንደተከበረ በአፍሪካውያን ሰማይ ስር በከፍታ የሚኖር የሰው ልጆች የእኩልነት ሚዛን እንደሆነ በመፅሐፉ በጉልህ ሰፍሯል፡፡
በመለሰ ተሰጋ