AMN – የካቲት 22/2017 ዓ.ም
የዓድዋ ድል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ደማቅ ታሪካዊ ድል መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ 129ኛው የዓድዋ ድል በዓል ምክንያት በማድረግ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ለመላው የፖሊስ ሠራዊት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ፖሊስ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ለሕዝቦቿ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ እንዲሁም ለህገ-መንግሥት መጽናት፣ የታላቁ የዓድዋ ድል የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና ተላብሶ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ሀገራችን ወደ ከፍታ ማማ እንድትገሰግስ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል ብሏል በመልዕክቱ፡፡
ቅድመ አያቶቻችን ያለ አንዳች ልዩነት በአንድነት ለሀገራችን ሉዓላዊነትና ክብር ሲሉ በጋራ የተዋደቁና የጋራ ድል ያስመዘገቡበት በመሆኑ የዓድዋ ድል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ደማቅ ታሪካዊ ድል መሆኑንም አመላክቷል፡፡
የዓድዋ ድል የብሔራዊ ኩራታችን ምንጭ ሲሆን ከኢትዮጵያም አልፎ የመላ ጥቁር ሕዝቦች ድል፤ ኩራትና የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሀገራችንን ፖሊስ አንድነት የበለጠ በማጎልበት፣ ጠንካራ የአሸናፊነት ሥነ-ልቦናን በመላበስ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በጀግንነት፣ በጽናት፣ በታላቅ ሀገራዊ ፍቅርና ስሜት በመፋለም በከፈለው መስዋዕትነት የኢትዮጵያን የህልውና አደጋ በማስወገድ ሉዓላዊነቷን እያስከበረ ይገኛልም ብሏል።
የፖሊስ ሠራዊታችን ለሚያጋጥሙት ፈተናዎች በቂ ምላሽ መስጠት የሚያስችለው ቁመና ላይ ሆኖ ፖሊሳዊ የሙያ መርህን በመከተል፣ የዕዝ ሰንሰለቱን ጠብቆ ለሀገራችን ሰላምና ደህንነት እንቅፋት የሆኑ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመከላከልና በመቆጣጠር በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየሰራ መሆኑንም አመላክቷል፡፡
እንደ ፖሊስ የዓድዋን ድል በዓል ስናከብር የዓድዋ ጀግኖች የአመራር ጥበብን፣ የውጊያ ስትራቴጂና ስልትን፣ የሎጀስቲክስ አስተዳደር እና የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና እሴቶችን በተሞክሮነት በመውሰድ፣ ለፖሊስ ሠራዊት ግንባታ በመጠቀም አዳዲስ ስኬቶችንና ድሎችን በማስመዝገብ የግዳጅ አፈፃፀም ጥራት እያረጋገጠ በመቀጠል የኢትዮጵያን ብሄራዊ ክብርና ተቋማዊ ሪፎርም አጠናክሮ ይቀጥላል ሲል መልዕክት ማስተላለፉን ከፌዴራል ፓሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡