የዘመናዊ ከተማነት ማሳያው ፈርጥ
የአዲስ አበባ መለያ መልክ ከሆኑና ከቀደምት ሰፈሮች መካከል አራት ኪሎ አንዱ ነው፡፡ አራት ኪሎ ልክ እንደነ ዘበኛ ሠፈር፣ ደጃች ውቤ፣ ሠባራ ባቡር፣ አፍንጮ በር፣ ስድስት ኪሎና መሰል የመዲናዋ ሰፈሮች ዝነኛና ዕድሜ ጠገብ ነው፡፡ ይሁንና ሁኔታውና ንጽህናው ስምና ክብሩን የሚመጥን እንዳልነበር ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ለከተሜው ሁነኛ መዝናኛ ቦታ የሆነው አራት ኪሎ በአካባቢው የሚገኙ ህንጻዎችም ቀለሞቻቸው የወየቡና የቀለም ወጥነት የጎደላቸው ስለነበሩ ውበታቸው ደብዝዞ ቆይቷል፡፡
ህገ ወጥ የጎዳና ንግድ የሚበረክትበት፣ እግረኛ መንገዱ ጠባብና ለእንቅስቃሴም የማይመች ሆኖ ለዓመታት ኖሯል፡፡ ከዚህ በፊት አካባቢው በህገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ የተጨናነቀ፣ መሸጋገሪያ ድልድዩ መዲናዋን የማይመጥንና ምቾት የሌለው ከመሆኑም ባሻገር ለአቅመ ደካሞች የማይመች፣ ለእግር ጉዞ የማይመች፣ የከተማዋን ገፅታም ጥላሸት የሚቀባ ነበር::
አራት ኪሎ የኮሪደር ልማት ከተሰኘ ድንቅ ሀሳብ ጋር ሲገናኝ ስምና ዝናውን ወደሚመጥን ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ ከሰሞኑ ተመርቆ ወደ አገልግሎት የገባው ‘አራት ኪሎ ፕላዛ’ የአካባቢውን ገጽታ ቀይሮታል፡፡ ከዚህ ቀደም በአዳባባዩ ዙሪያ ይታዩ የነበሩ የአራት ኪሎ መልከ ጥፉ ገጾች አሁን የሉም፡፡
የዝግጅት ክፍላችንም የኮሪደር ልማቱ ከፈጠራቸው ውብ ስፍራዎች መካከል አንዱ በሆነው አራት ኪሎ ፕላዛ ተገኝቶ እንደተመለከተው በውስጡ የሀገር ውስጥ አልባሳት፣ መዋቢያዎች፣ ወርቅና ብር መሸጫ ቤቶች፣ የስልክ መሸጫዎች፣ የፈጣን ምግብ አገልግሎት እና መሰል የንግድ አገልግሎቶችን መስጠት ጀምሯል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌታሁን አበራ በአራት ኪሎ ፕላዛ ምረቃ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፣ አካባቢው ከዚህ ቀደም ለተሽከርካሪ፣ ለእግረኞችና ለአካል ጉዳተኞች መተላለፊያነት አስቸጋሪ ነበር፡፡ አሁን ችግሩን በሚቀርፍና ዘመናዊነቱን በጠበቀ መልኩ ተገንብቷል፡፡ አካል ጉዳተኞችም በቀላሉ መተላለፍ የሚችሉበት የአሳንስር መጓጓዣ ተገጥሞለታል፡፡ ከተማዋን ውብ፣ ጹዱና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ በኮሪደር ልማት ስራው እየተደረገ ያለው ጥረት ማረጋገጫም ነው ብለዋል፡፡
አራት ኪሎ ፕላዛ በኮሪደር ልማቱ ተሰርተው ውብ ገፅታን ከተላበሱ የከተማዋ አካባቢዎች መካከል አንዱ ስለመሆኑ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉ የከተማዋ ነዋሪዎችም ተናግረዋል፡፡ ወጣት ሜላት አድነው አራት ኪሎ በተለምዶ ባሻ ወልዴ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ተወልዳ ማደጓን ጠቁማ፣ አካባቢው በርካታ ሰዎች የሚኖሩበት እንደመሆኑ ከፍተኛ መጨናነቅ የነበረበት መሆኑን ተናግራለች፡፡
አራት ኪሎ አደባባይ እና በዙሪያው የነበሩ መንገዶች ጠባብ ስለነበሩ ለእግር ጉዞ እምብዛም አይመችም ነበር የምትለው ወጣቷ፣ ከዚሁ መነሻነት እርሷና ጓደኞቿ ለመዝናናት ሲፈልጉ ወደ ሌሎቹ የከተማዋ ክፍሎች ይሄዱ እንደነበር ነግራናለች። “አሁን ግን በኮሪደር ልማቱ በየቦታው ወጣቶች ሊዝናኑባቸው የሚችሉ ስፍራዎች ተፈጥረዋል” ብላለች፡፡
አራት ኪሎ ፕላዛ የቀድሞውን የአካባቢውን የመጨናነቅ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል የምትለው ወጣቷ፣ ለዓይን የሚመች መልክም ፈጥሯል። በማታ አካባቢው በመብራት ስለሚደምቅ ደስ የሚል ድባብ አለው፤ የመንገድ ዳርቻዎችም በተለያዩ ዕፅዋቶች አሸብርቀዋል፤ በየጥጉ በሚገኙ መቀመጫዎች አረፍ ብሎ መንፈስን ማደስ የሚቻልበትን ዕድል ፈጥሯልም ብላለች፡፡
አቶ አዳሙ ለገሰም ነባር የአራት ኪሎ አካባቢ ነዋሪ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተከናወኑ የልማት ስራዎች ቀድሞ የነበረው የአካባቢው የማይመች ገፅታ አሁን ተቀይሯል ብለዋል፡፡ ከጆሊ ባር ወደ ትምህርት ሚኒስቴር አሊያም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ የሳይንስ ፋኩልቲ ለመሻገር ለእይታ በማይመችና ለደህንነት በሚያሰጋ የብረት ድልድይ አማካኝነት ነበር የምንሻገረው ብለው፣ አራት ኪሎ ፕላዛ በአካባቢው የነበረውን የማይመች እንቅስቃሴ ቀይሮታል ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ ለቀጣዩ ትውልድ የሚሆን ዐሻራዎችን እያስቀመጠች ትገኛለች የሚሉት አራት ኪሎ ፕላዛ ውስጥ በሚገኙ ሱቆች ሲገበያዩ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሰርካለም ታደሰ ናቸው፡፡ ወይዘሮዋ በሰጡን አስተያየት፣ “የኮሪደር ልማቱ እንደዚህ አይነት ፕላዛዎችን ከማስገኘቱም በተጨማሪ ልጆቻችንን የት ወስደን እናዝናና? ከሚል ጭንቀት የሚገላግሉ በርካታ ውብ የመዝናኛ ስፍራዎችን ፈጥሮልናል” ብለዋል፡፡
አሁን ልጆቻችን ያላንዳች ውጣ ውረድ በየመንገዱ ዳር ቁጭ ብለው የሚዝናኑባቸውና የሚጫወቱባቸው የመዝናኛ ስፍራዎች ተዘጋጅተዋል ያሉት ወይዘሮ ሰርካለም፣ በተለይ ፋውንቴኖች ወይም ፏፏቴዎች እና ልጆች ቁጭ ብለው ሻይ ቡና የሚሉባቸው የመዝናኛ ስፍራዎችም በየሰፈሩ ተፈጥረዋል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ነጻነት ዳባ በበኩላቸው፣ የመተላለፊያና የመዝናኛ ስፍራው በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የህዝብ እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረገ ብቁ አገልግሎት እንዲሰጥ ሆኖ መገንባቱን ተናግረዋል።
ስፍራው እግረኞች በቀላሉ የሚያልፉበት ብቻ ሳይሆን አረፍ ብለው የሚዝናኑበትና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት የሚያገኙበት መሆኑንም ጠቁመው፣ ኮርፖሬሽኑ የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት ከመሆኑ አኳያ የአራት ኪሎ ፕላዛ የምድር ውስጥ መተላለፊያና መዝናኛ ስፍራን ተረክቦ በማስተዳደር ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ ያደርጋል ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ይዞላት በመጣው በረከት እንደ ንስር እራሷን እያደሰች የውበት ብርሃኗን መፈንጠቅ ጀምራለች፡፡ በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት የበርካቶችን ቀልብ ገዝታ የዓለም ታላላቅ ተቋማትን ሳይቀር እንደ ማግኔት ስባ ጉባኤዎችን ያስተናገደችው ይህች ከተማ አሁንም የበለጠ ለመድመቅ በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ምዕርፍ ላይ ትገኛለች፡፡
የ4 ኪሎ ፕላዛ ከዚህ ቀደም የነበረውን የአካባቢውን ገፅታ ከመቀየርም ባለፈ ዘመናዊ የመገበያያ ስፍራዎች፣ መሸጋገሪዎችን እና መዝናኛ ስፍራዎችን አካትቶ መገንባቱ ከተማዋ እየሄደችበት ላለው የዘመናዊነት ጉዞ እንደ አንድ ፈርጥ መሆኑን በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይን እና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት ሰዎች ምቾት በሌለው ድልድይ ይሻገሩ ነበር፣ መሻገሪያው ለአቅመ ደካሞች የማይመች፣ ለእግር ጉዞ የማይመች፣ በከተማዋ ገፅታ ላይም ጥላሸት የሚቀባ ነበር ያሉት ዳንኤል (ዶ/ር)፣ ይህ መልኩ አሁን ተቀይሮ ዘመናዊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበትና አማራጭ የመዝናኛ ስፍራ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይህም አዲስ አበባ እየዘመነች ለመምጣቷ ማሳያ ፈርጥ ነው የሚል ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡
ደራሲውና የከተማ ልማት ባለሙያው አውስትራሊያዊው ጄ.ፒ. ጎድርድ ፕላዛዎች በከተሞች ዕድገት ላያ ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን “ሰብ ሰርፌስ ደቨሎፕመንት ኢን ዘ አርባን ኢንቫይሮንመንት” በተባለ ጥናታዊ ፅሁፋቸው አስፍረዋል፡፡ በዓለም ላይ እንደ ሆንግ ኮንግ፣ ማድሪድና የቻይናዋ ጓንግዙ ከተሞች በዚህ ረገድ በትልቁ ስለመስራታቸው ነው ጥናቱ የሚያትተው፡፡
በከተማ የሚሰሩ የውስጥ ለውስጥ መዝናኛዎች የተለመዱና ለከተሜነት መለያ መሆናቸውንም በመጠቀስ ይህም፣ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ይዘረዝራል። በተለይም የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ፣ የበለጠ ንጹህ እና ለአካባቢ ተስማሚና ምቹ የቦታ አጠቃቀምን ለመፍጠር፣ ለእግረኞች ደህንነቱ የተጠበቀ መሸጋገሪያ ለመፍጠር አይነተኛ ሚና ይጫወታሉ ይላል፡፡
በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2030 በዓለም ላይ በከተማ የሚኖረው ህዝብ ቁጥር ወደ 61 በመቶ ከፍ ሊል እንደሚችል በመፅሐፉ ተገልጿል፡፡ ይህም የከተማ ቦታዎችን ለተለያዩ ተግባራት አብቃቅቶ መመደብና መጠቀም ግድ የሚልበት ወቅት መደረሱን አመላካች ነው፡፡ በከተሞች የሚሰሩ ፕላዛዎች የንግድ ስርዓትን ከማዘመንና የከተሜነት መንፈስን ከመከሰት ባሻገር ጎብኝዎችን በመሳብ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ ያደርጋሉም ይላል፡፡
በኮሪደር ልማት ስራ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሕንጻዎች እንዲታደሱ ተደርጓል፤ የከተማዋን ደረጃ የሚመጥኑ መንገዶች እና እግረኛ መንገዶች ተገንብተዋል፤ የመንገድ ዳር መብራቶችም እየተተከሉ ነው፡፡ በጥቅሉ የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና ምቹ እያደረጋት ይገኛል፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ