የዩኒቨርሲቲዎች በጀት ባስመዘገቡት ውጤት ልክ የሚመደብ ይሆናል -ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

AMN – ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም

ዩኒቨርሲቲዎች የሚመደብላቸው በጀት ባስመዘገቡት ውጤት ልክ እንደሚሆን የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለፁ።

በትምህርት ዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በተቀናጀ መልኩ ማሻሻል የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል።

ስምምነቱን ትምህርት ሚኒስቴርና 47 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የቦርድ ሰብሳቢዎችና የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ፈርመውታል።

የትምህርት ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት፥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በመሰረታዊነት ለመቀየር የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በተለይም ብቃት ያለው የሰው ሃይል ለማፍራትና ፋይዳቸው የጎላ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ለማውጣት ጥራት ላይ መስራት ግዴታ መሆኑ በስምምነቱ ተካቷል ብለዋል።

ስምምነቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በትክክለኛ መንገድ የሚሰሩና ተጠያቂነት ያለባቸው እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ሀገር የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በሳይንሳዊ ምርምር የሚያግዙ መሆን እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት።

በሀገር የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑና የዜጎችን ህይወት እንዲቀይሩ ሁሉም ተቋም ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች የሚመደብላቸው በጀት ባስመዘገቡት ውጤት ልክ ይሆናል ያሉት ሚኒስትሩ፥ ዝቅተኛ አፈፃፀም ያስመዘገቡ እኩል በጀት የሚመደብበት አሰራር ይቀራል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች የተጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃትና በጥራት እንዲፈፅሙ በተለይም ሙስናን ማጥፋት ግዴታ መሆኑንም አንስተዋል።

ሙስና የትውልድ ጸር በመሆኑ ለትውልዱ አርዓያ የሚሆን ዩኒቨርሲቲ መፍጠር እንደሚገባም ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review