የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትግበራ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከ42 ሚሊየን በላይ ማድረስ አስችሏል ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

AMN-ታህሳስ 5/2017 ዓ.ም

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከ42 ሚሊዮን በላይ ማድረስ ማስቻሉን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ስትራቴጂው ያለበትን ክፍተት በመለየት አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እየተዘጋጀ መሆኑን ተገልጿል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን አለማየሁ(ዶ/ር) እንዳሉት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ የሪፎርም ስራዎች እንዲፋጠኑ አድርጓል።

ባለፉት አራት አመታት በነበረው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የቴሌኮም ዘርፉ ለግል ባለሃብቶች ክፍት መደረጉንና የ10 በመቶ ድርሻውንም ለአክስዮን ሽያጭ እንዲቀርበ መደረጉ ዘርፉ በፍጥነት እንዲያድግና ተደራሽ እንዲሆን ካደረጉት መካከል ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መተግበር የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከ17 ሚሊዮን ወደ 42 ሚሊዮን በላይ እንዲደርስ አድርጓል ነው ያሉት።

ስትራቴጂው የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ጨምሮ በመንግስት እና በግል የሚገነቡ የዳታ ማዕከላት ቁጥርንም ማሳደግ ማስቻሉን ጠቅሰዋለ።

በአይ ሲ ቲ ፓርክ ከፍተኛ አቅም ያላቸው የዳታ ማዕከላት መገንባታቸውም የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን አብራርተዋል።

በፓርኩ ባለፉት አራት አመታት በተከናወኑ ተግባራት ለኢንቨስትመንት፣ ለስራ እድል ፈጠራ፤ ተሰጥኦን ማበልፀግና ልምድ መለዋወጥ የሚያስችሉ ምቹ መደላድ ተፈጥሯል ብለዋል።

በርካታ የመንግስት አገልግሎቶችንም በኦንላይን መስጠት የሚያስችል ስራ መሰራቱን አመልክተዋል።

የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ መርሃ-ግብርን ጨምሮ ዲጂታል ክህሎት ያለው ማህበረሰብ ለመፍጠር በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስራዎች በዋናነት በፌዴራል ተቋማትና በዋና ከተሞች ሲሰራ እንደነበር ጠቅሰዋል።

የሳይበር ምህዳሩን ለመጠበቅ በመንግስት በኩል እየተሰራ መሆኑን ገልፀው ማህበረሰቡም በዚህ ረገድ ያለውን እውቀትና ክህሎት በየጊዜው ማሳደግ እንዳለበት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review