
AMN – ታኀሣሥ 25/2017 ዓ.ም
ጥምር የፀጥታ አካላት አመራር የ2017 ዓ.ም የገና በዓል የፀጥታ ማስከበር ተግባራትን አስመልክቶ በአዲሰ አበባ ፖሊስ ሠላም አዳራሽ ለአመራሩ የሥራ መመሪያ ተሰጥቷል።
በመድረኩ የህግ ማስከበሩን ሥራ በውጤት ለማከናውን የሚያስችል ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ውይይቱን የመሩትና መመሪያ የሰጡት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ም/ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ባስተላለፉት መልዕክት በዓላት ሲከበሩ አሉታዊ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች እንደመልካም አጋጣሚ እንዳይጠቀሙበት ከሚከናወነው መደበኛ የወንጀል መከላከል ስራ ጎን ለጎን የህብረተሰቡን አቅም መጠቀም ፈፅሞ መዘንጋት የሌለበት ሥራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ቅንጅታዊ የሥምሪት አቅጣጫን በመከተል ጠንካራ የወንጀል መከላከል ተግባር ማከናወን እንደሚገባም ተናግረዋል።
የፀጥታ አካላቱ ዋና ግብ በህግ የበላይነት ሠላምና ፀጥታን ማረጋገጥ በመሆኑ ሁሉም አመራርና አባል ይህን ተገንዝቦ በዓሉ በስኬት እንዲከበር እንደ ከዚህ ቀደሙ ኃላፊነቱን በብቃት ሊወጣ እንደሚገባ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው፣ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ተቀናጅቶ በመስራቱ ስኬታማ መሆን እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
የከተማዋን ሠላምና ፀጥታ በማረጋገጥ በኩል የድርሻውን እየተወጣ የሚገኘው የሠላም ሠራዊት እንደ ሁልጊዜው ከፀጥታ አካላቱ ጋር ተቀናጅቶ ኃላፊነቱ ለመወጣት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
በዓሉ በስኬት እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ለማስቻል ከማህበረሰቡ፣ ከኃይማኖት አባቶች እና የበአሉ ጉዳይ ከሚመለከታቸው አደረጃጀቶች ጋር መድረክ ተዘጋጅቶ ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
የመረጃ ሥርዓትን በማጠናከር የሥምሪት አቅጣጫን ከበዓሉ አከባበር ሁኔታ አንፃር በማየት የሥምሪት አቅጣጫ መከተል እንደሚገባ ያስገነዘቡት ደግሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ናቸው፡፡
የገና በዓልን በተመለከተ ከሚከናወኑት ቅድመ ወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከል ሥራዎች ባሻገር ለፀጥታ ስጋት የሆኑ ቦታዎችን በጥናት በመለየት ጠንካራ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በእምነት ቦታዎች፣ በገበያ ስፍራዎች፣ በመዝናኛና በትራንስፖርት መጠበቂያ ስፍራዎች እና ሌሎች የህዝብ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ግርግሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ወንጀል ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ለመቆጣጠር በቂ የፀጥታ ኃይል መመደቡን እና የፀጥታ ስራው በቴክኖሎጂ እየታገዘ እንደሚከናወንም ገልጸዋል፡፡
በግብይት ወቅት የሚከሰቱ የስርቆት ወንጀሎችን፣ የሀሰተኛ ገንዘብ ኖት ስርጭት እንዲሁም ህገ-ወጥ የዋጋ ንረትን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች እና በዓሉ በስኬት እንዲከበር ለማስቻል ህብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን ሊያደርግ እንደሚገባ ኃላፊዎቹ አሳስበዋል፡፡
አልኮል ጠጥተው የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ከሚደረገው ቁጥጥር ባሻገር ለመንገድ ትራፊክ አደጋ በሚያጋልጡ ደንብ መተላለፎች ላይ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ በውይይቱ ላይ ተገልጿል።
በዓሉ የሠላምና የደስታ እንዲሆን መላው የፀጥታ ተቋማት መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡
ህብረተሰቡ ለሠላም እንቅፋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት በ011-1-26-43-59 ፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡