የጋምቤላ ከተማ የኮሪደር ልማት የገቢ ማሰባሰቢያ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።
የጋምቤላ ከተማ የኮሪደር ልማት የመጀመሪያው ምዕራፍ በመከናወን ላይ ይገኛል።
በልማቱ መላው ሕዝብ ተሳታፊ ይሆን ዘንድ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ አስፈላጊ ሆኗል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ እንደገለፁት የኮሪደር ልማቱ መሰራት የከተማዋን ገፅታ አጉልቶ የሚያወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ልማቱን ለማከናወን በመንግስት በጀት ብቻ ማጠናቀቅ ስለማይቻል መላው ሕዝብ ታሪካዊ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በመሆኑም መላው የክልሉ ሕዝቦች፣ በክልሉ በተለያዩ ሥራዎች የተሰማሩ ባለሀብቶች፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች፣ ከክልሉ ውጭ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያሉ የጋምቤላ ክልል ተወላጆችና የጋምቤላ ከተማን ኮርደር ልማት ለመደገፍ ፍቃደኛ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ ዶክተር ሳይመን ሙን በበኩላቸው በጋምቤላ ከተማ ደረጃውን የጠበቀ የኮሪደር ስራን ለማከናወን የተጀመረውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መጠየቃቸዉን ከክልሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡