የግብይት ስርዓቱን በዘላቂነት ለማስተካከል በጥናት ላይ ተመርኩዞ በተከናወነ ስራ በርካታ ህገ ወጥ የሆኑ አሰራሮች መኖራቸውን ተመልክተናል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ኅዳር 10/2017 ዓ.ም

እንደ ሀገር ያለውን የግብይት ስርዓት በዘላቂነት ለማስተካከል በጥናት ላይ ተመርኩዞ በተከናወነ ስራ በርካታ ህገ ወጥ የሆኑ አሰራሮች መኖራቸውን ተመልክተናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 4ተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡

የመዲናዋን የግብይት ስርዓት በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡

በመርካቶ ህጋዊ ግብይት እንዲደረግና ለእያንዳንዱ ግብይት ነጋዴው ደረሰኝ እንዲቆርጥ በጥናት ላይ የተመሰረተ ቁጥጥር እና ክትትል የማድረግ እንቀስቃሴ መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡

መርካቶ ትልቁ የገበያ ስፍራ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ ለኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ቢሆንም ነገር ግን ለህገወጥነት መደበቂያ ቦታ ሆኗል ብለዋል፡፡

በመሆኑም መርካቶን ወደ ህጋዊ የንግድ ስርዓት ለማስገባት በእውቅት ላይ የተመሰረተ ጥናት ሲደረግ መቆየቱን በማስታወስ በጥናቱም አብዛኛው የሚመለከታቸው የግብር ሰብሳቢ መስርያ ቤቶች ፊት ለፊት የሚታዩት ላይ ትኩረት ማድረጋቸው መረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡

ጥናቱን ተከትሎ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውይይት መካሄዱንም ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ግብር መክፈል የለብንም የሚል ሙግት አላጋጠመንም ነው ያሉት ከንቲባዋ፡፡

እንዲሁም ግማሹ ግብር እየከፈለ ሌላው የማይከፍልበት አሰራር መኖሩን ተገንዝበናል ብለዋል::

ግብር ለማስከፈል እና ደረሰኝ እንዲቆርጡ ለማድረግ በተደረገው ሂደት በሀሰት ውዥንብር በመንዛት መጋዘኖችን በመዝጋት በምሽት እቃዎች ሲጫኑ እንደነበርም ጠቁመዋል::

በተሰበሰበው ገንዘብ የህዝብን ጥያቄ እየመለስን ነው ያሉት ከንቲባዋ ግብር መክፈልና ደረሰኝ መቁረጥ ግዴታ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የንግዱ ማኅበረሰብ ኃላፊነቱን እየተወጣ የሚሰርቅና የሚያጭበረብር የመንግስት አካልን አጋልጦ እንዲሰጥም ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመተማመን መስራት ሀገርን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ያነሱት ከንቲባዋ በቀጣይም ህጋዊ ስርዓት በመዘርጋት እና ለእያንዳንዱ ግብይት ደረሰኝ እንዲቆረጥ በማድረግ ግብርን በአግባቡ የመሰብሰብና ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review