የጥምቀት በዓል አከባበር በተለያዩ የዓለም ሀገራት

You are currently viewing የጥምቀት በዓል አከባበር በተለያዩ የዓለም ሀገራት

AMN – ጥር 11/2017 ዓ.ም

የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ተጉዞ በቅዱስ የሐንስ እጅ የተጠመቀበትን ዕለት በማስታወስ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው።

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ በተለይም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እና በካቶሊክ እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ እና ዋነኛው ነው።

በዓሉ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ አንድነት እና ሀገራዊ ባህሎች ጎልተው የሚታዩበት፣ በርካታ ትኩረት የሚስቡ ኩነቶችም የሚስተዋሉበት ነው።

የጥምቅት በዓል በሌሎች የዓለም ሀገራትም በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል። በዓሉን ለየት ባለ መልኩ የሚያከብሩ ሀገራትን እንመልከት።

ከ90 ሚሊዮን በላይ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እንዳሏት የሚነገርላት ሩሲያ የጥምቀት በዓልን በድምቀት ከሚያከብሩ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናት።

የሩሲያ፣ የግሪክ እና የቡልጋሪያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቅን እና ሥላሴዎችን ለማስታወስ በበረዶ ውኃ ውስጥ ራሳቸውን ሦስት ጊዜ ይነከራሉ።

በእነዚህ ሀገራት የሚገኙ ኦርቶዶክሳዊያን ይህን የሚያደርጉት ታዲያ ከኃጢአታቸው እንደሚያነፃቸው በማመንም ጭምር ነው።

በተለይ በቡልጋሪያ ቄሶች ጉድጓድ ውስጥ ባለው ቀዝቃዛ ውኃ ላይ መስቀሉን ሲወረውሩ በከበሮ የታጀበ ባንድ የዜማ ድምፅ ማሰማት ይጀምራል፤ ሌሎችም በዳንስ እና በጭፈራ ሁነቱን ያደምቁታል።

በተወሰኑ የአውሮፓ ሀገራት የሚገኙ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችም በጥልቁ ቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ በዋና ውድድር የታጀበ የጥምቀት በዓልን ያሳልፋሉ።

በቱርክ፣ በቦስኒያ እና ሄርዞጎቪኒያ የሚገኙት የእምነቱ ተከታዮች በቄሶች ወደ ውኃ የተጣለውን የእንጨት መስቀል ለመያዝ የዋና ፉክክር ያደርጋሉ።

በዋና ውድድሩ መስቀሉን መያዝ የቻለ ሰው ዓመቱን በሙሉ የተባረከ ይሆናል ብለው ያምናሉ።

በተለይም ቱርኮች ይህ ሥርዓት ጤና እና ብልፅግናን ያመጣል የሚል እምነት አላቸው። በዚህ ሥርዓት መሳተፍ የክብር እና ጥንካሬ ምልክት ተደርጎ ይቆጠራል።

በላቲን አሜሪካ፣ በፊሊፒንስ እና በስፔን ጥምቀት “ኤፒፋኒ ዲያ ዴ ሎስ ሬየስ ማጎስ” በመባል ይጠራል። በዓሉ ለልጆች ስጦታ በማበርከት ይከበራል።

በስፔን እና በብዙ የላቲን አሜሪካ ሀገሮች የገና ስጦታዎች የሚሰጡት በዚህ በዓል ወቅት ነው። ልጆች በበዓሉ ዋዜማ ለሰብአ ሰገል ደብዳቤዎችን ይጽፋሉ።

ሕፃናት ስጦታ ለማግኘት በዋዜማው ምሽት ከቤታቸው ውጭ ጫማቸውን ያሳድራሉ።

በሜክሲኮ ያለው የጥምቀት በዓል የአከባበር ልማድ ደግሞ የተለየ ነው። በቀለበት ቅርፅ እና በውስጡ በማይታይ መልኩ የኢየሱስ ምስል የተሠራበት እና ዘውድ ያጠለቀ ጣፋጭ ኬክ መመገብ በሜክሲኮ የተለመደ ነው።

በኬኩ መሐል በድብቅ የተሠራው የክስርቶስ ምስል ሕፃኑን ኢየሱስ ከንጉሥ ሄሮዶስ ለመሰወር የተደረገውን ለማሳየት ሲባል የሚደረግ መሆኑ ይገልጻል።

ይዘቱ እና መልኩ ቢለያይም በአሜሪካ እና ፈረንሳይም የበዓሉ አከባበር ልማድ ከሜክሲኮው ጋር ተመሳሳይ ያለው ነው።

በአየርላድ ደግሞ የጥምቀት በዓል ሴቶች እፎይታን የሚያገኙበት ነው። ከብዙ የሥራ ድካም አርፈው የሚያከብሩት በመሆኑም ትንሹ ገና ወይም በተለምዶ የሴቶች ገና በማለት ይጠሩታል።

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review