AMN – ጥር 10/2017 ዓ.ም
የጥምቀት በዓልን በትህትና እና አብሮነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ማክበር እንደሚገባ ተገልጿል።
የጥምቀት በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በአደባባይ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ነው።
የጥምቀት ክብረ-በዓል በሰው ልጅ ወካይ በማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የተመዘገበ የኢትዮጵያ ሀብት መሆኑም ይታወቃል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ መጋቢ ሃዲስ ፀጋዬ ወልደተንሳኤ እንደገለጹት፤ ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ መጠመቁን አስመልክቶ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የሚከበር በዓል ነው።

የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ ተጠምቆ አርአያ የሆነበት በመሆኑ ትህትናን እና አብሮነትን በመግለጥ ማክበር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ጥምቀት የአደባባይ በዓል እንደመሆኑም ከኃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ ባህላዊና ማህበራዊ ትስስር በማጠናከር በድምቀት የሚከበርና ኢትዮጵያዊ እሴት የሚታይበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም ምዕመኑ የጥምቀት በዓልን በአንድነት፣ በፍቅርና በትህትና ከማክበር ባሻገር በዘወትር ተግባራትም ይበልጥ የሚጠናከሩበት በዓል መሆኑን ነው የገለጹት።
በዓሉ አንዳችን ለአንዳችን ፍቅርን፣ ወዳጅነትንና ለዘላቂ ሰላም ትብብራችን የሚታይበት ሊሆን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

አርቲስት ሙሉነህ ዘለቀ በበኩሉ፤ እርስ በእርስ በመተጋገዝ፣ በመከባበርና አንዱ ለሌላው አለኝታ መሆንን በማረጋገጥ በዓሉን ማክበር ይገባል ብለዋል።
በዓሉ ኢትዮጵያን የምናስተዋውቅበትና ለወጣቶች መልካም እሴትን የምናወርስበት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የታቦታትን ማደሪያ የፅዳት መርሃግብር ላይ የተገኙት የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆኑት አቶ ቢላል ሙሄ በበኩላቸው የጥምቀት በዓልን የተለያዩ እምነት ተከታዮች ያለንን መከባበርና መተባበር በተግባር የምናሳይበት ነው ብለዋል፡፡
በዓሉን ለሚያከብሩ ምዕመናን የውሃ፣ የምግብና ሌሎች አቅርቦቶችን በማድረግ ኢትዮጵያዊ ባህላችንን የምናንጸባርቅበት ነው ሲሉም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡