የፈላ ውሀ ሰውነቷ ላይ በመድፋት ከባድ የአካል ጉዳት ያደረሰው ግለሰብ በ7 ዓመት ከ5 ወር ፅኑ እስራት ተቀጣ

You are currently viewing የፈላ ውሀ ሰውነቷ ላይ በመድፋት ከባድ የአካል ጉዳት ያደረሰው ግለሰብ በ7 ዓመት ከ5 ወር ፅኑ እስራት ተቀጣ

AMN – መጋቢት 10/2017

ከጎረቤቱ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት የፈላ ውሀ ሰውነቷ ላይ በመድፋት ከባድ የአካል ጉዳት ያደረሰው ግለሰብ በ7 ዓመት ከ5 ወር ፅኑ እስራት መቀጣቱን የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገለፀ።

ተከሳሽ ሀብታሙ ተክለማሪያም ወንጀሉን የፈፀመው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ኮንጎ ሠፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።

የግል ተበዳይና ተከሳሽ በአንድ ግቢ ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን፣ በሁለቱ ግለሰቦች መካከል በንግግር የተፈጠረን አለመግባባት ቂም በመያዝ የግል ተበዳይ ግቢ ውስጥ ቁጭ ብላ ስራዋን እየከወነች ባለችበት ወቅት ተከሳሽ በጀርባዋ በኩል በመሄድ የፈላ ውሀ ደፍቶባት ከባድ የአካል ጉዳት በማድረሱ በቁጥጥር ስር መዋሉን በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የኮልፌ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አስታውቋል፡፡

ፖሊስ የተፈፀመውን ወንጀል መነሻ በማድረግ ተገቢውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ በማደራጀት በዐቃቤ ህግ በኩል ክስ እንዲመሰረትም አድርጓል፡፡

የወንጀል ምርመራ መዝገቡን ሲከታተል የቆየው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አዲስ ከተማ ምድብ ፈጣን ችሎት የካቲት 25 ቀን 2017 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ሀብታሙ ተክለማሪያም በ7 ዓመት ከ5 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡

የግል ተበዳይ በተፈፀመባት ወንጀል ለከባድ የአካል ጉዳት መዳረጓን በማንሳት፣ ተከሳሽ በህግ ፊት ቀርቦ ተገቢው እርምጃና ቅጣት የተላለፈበት መሆኑ እንዳስደሰታት ገልፃለች።

በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ማናቸውንም ጥቃቶች አስቀድሞ መከላከልም ሆነ ተፈፅሞ ሲገኝ አስፈላጊውን መረጃ ለሚመለከተው አካል በመስጠት በኩል ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪ ማቅረቡን ከከተማዉ ፖሊስ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review