የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የምክር ቤቱ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሣችሁ! አደረሠን!
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መዳን ሲል መከራን ተቀብሎ በመስቀል ላይ ተሰቅሎና ቤዛ ሆኖ እውነተኛ ፍቅሩን ለሰው ልጆች ገልጿል ፤ ሞትን ድል አደርጎ በመነሳት የሰውን ልጅ ከዘላለማዊ ኃጢያት ነፃ አውጥቷል፡፡ እሱ በከፈለው መስዋዕትነት ለሰው ልጅ ሁሉ መዳን ሆኗል።
ስለሆነም የክርስትና እምነት ተከታዮች ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መዳን ሲል የከፈለውን መከራ፣ ስቃይና ከሕማማቱን እያሰቡ በየዓመቱ ትንሣኤውን ያከብሩታል።
በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ የስቅለትና የትንሳኤ በዓል ልዩ ሥፍራ ይይዛል። ረጅሙን የዐብይ ፆም ወራት በፆም በፀሎት አሳልፈው ፤ አርብ ላይ ሆነው እሁድ ትንሳኤውን እያሰቡ ሰሙነ ሕማማቱን እጅግ ውብ በሆኑ ሐይማኖታዊ ሥርዓቶችን አሳልፈው በዓለ ፋሲካን ያከብራሉ ፡፡ በተመሣሳይ በሌሎች ቤተ እምነቶችም እንዲሁ የዓብይ ፆም ግዜን በፆምና በፀሎት የሚሳልፉ ሲሆን የትንሣዔ በዓሉንም በልዩ ልዩ መልኩ ያከብሩታል።
የትንሣኤ በዓል ወይም የፋሲካ በዓል የፀብ ግድግዳ ፈርሶ በፈጣሪና በሰው ልጆች መሀል እርቅ የሆነበት ፣ የሰው ልጆች ምህረት ያገኙበት ፣እውነተኛ ሠላምና ደስታ የተገለፀበት ነው፡፡
ስለሆነም የፋሲካ በዓልን ስናከብር በይቅርታ፣ በምህረትና በዕርቅ ውስጥ ሆነን ሊሆን ይገባል።
በፆሙ ወራት ያሳየነውን መልካም ተግባራትን በማጠናከር ያጡና የተቸገሩ ወገኖችን በማሳብና ፍቅር በመስጠት፣ የኢትዮጵያን ሠላም በሚያፀኑና አብሮነታችንን የሚያጠናክሩ ተግባራትን በማከናወን ልናከበር ይገባል፡፡
በዓሉ የሠላም የፍቅርና እውነተኛ ደስታ የሚገለፅበት እንዲሆን ምክር ቤቱ ይመኛል!