የፌዴራል ፖሊስ ውጤታማ የለውጥ ስራዎቹ ዓለምአቀፍ እውቅና እያስገኙ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ቸኮል ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ በዓለም አቀፍ የፖሊስ ጉባኤ ላይ ምርጥ የፖሊስ መተግበሪያ ተብሎ በአንደኝነት መሸለሙ ይታወቃል።
እንዲሁም ከዱባይ ፖሊስ ጋር በመተባበር ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል በተሰራው ውጤታማ ስራ የሜዳልያ ተሸላሚ ሆኗል።
ሽልማቶቹን በማስመልከት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ቸኮል መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም የፌዴራል ፖሊስ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።
በፖሊስ ምርመራ እና ወንጀል መከላከል ላይ ያተኮሩ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን በአብነት ጠቅሰው፤ በዚህም በቴክኖሎጂ በታገዘ ወንጀል መከላከል ስራ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ውጤታማ የለውጥ ስራዎቹ ዓለም አቀፍ እውቅና እያስገኙ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለአብነትም የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ ምርጥ የፖሊስ መተግበሪያ ተብሎ መሸለሙን አንስተዋል።
ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል ዙሪያ የተሰራው ውጤታማ ስራም እውቅና መገኘቱን አመልክተዋል።
ፌዴራል ፖሊሲ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ውጤታማ የወንጀል መከላከል እና ዘመኑን የዋጀ የምርመራ ስራን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ በቅርቡም ስራውን የሚያቀላጥፉ ቴክኖሎጂዎች ወደ ስራ እንደሚያስገባ ተናግረዋል።
የፌዴራል ፖሊስ የቴክኖሎጂ ማስፋፊያ መምሪያ ሀላፊ ኮማንደር ደምሴ ይልማ በበኩላቸው፤ የፌዴራል ፖሊስ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ ወንጀልን በመከላከል ባስገኘው ከፍተኛ ውጤት ተሸላሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ሽልማቶቹ ፌዴራል ፖሊስ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖለጂ በመጠቀም በዘርፉ የደረሰበትን ደረጃ የሚያሳይ አኩሪ ውጤት መሆኑን ጨምረው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ፖሊስ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉትን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በቀጣይም ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረ እየሰራ መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል።