AMN – ጥር 16/2017 ዓ.ም
የአየር ትራንስፖርት ደህንነትን አስተማማኝ ለማድረግ የአቪዬሽን ዘርፉን በሁሉም ረገድ የማዘመንና የማጠናከር ስራ መሰራቱን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ ገለፁ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም ባለስልጣኑ የሲቪል አቪዬሽን ዘርፍ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዲስፋፋና እንዲያድግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዘርፉ ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አስረድተዋል ።
ባለሥልጣን ባለፉት 80 ዓመታት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ በኤር ናቪጌሽን አገልግሎት ውጤታማ ስራ ማከናወኑን አውስተዋል።
ባለስልጣኑ በኢትዮጵያ የአየር ክልል ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም በረራ ደኅንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ እንዲሆን ማስቻሉን ገልጸዋል።
የአየር ትራንስፖርት ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝነቱ የተረጋገጥ እንዲሆን የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ በዚህ ረገድ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ትኩረት አድርጓል ብለዋል።
ባለስልጣኑ በአካዳሚና በቴክኒክ ብቁ የሰው ሃይል ማፍራት መቻሉን ገልፀው፤ ዘንድሮ ብቻ 100 የአየር ትራፊክ ባለሙያዎች ለማሰልጠን ማቀዱን ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ የመጪውን ዘመን የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ታሳቢ ያደረገ የ15 ዓመት ብሔራዊ የኤር ናቪጌሽን ዕቅድ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።