ዲጂታል ኢትዮጵያ ዕውን እንዲሆን የሳይበር ደህንነትን የማረጋገጥ ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው -የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር

AMN-ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም

ዲጂታል ኢትዮጵያ ዕውን እንዲሆን የሳይበር ደህንነትን የማረጋገጥ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት ሀሚድ አስታወቁ።

ለ5ተኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው አገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ዛሬ በድሬደዋ በፓናል ውይይት እየተከበረ ነው።

በዚሁ ጊዜ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት ሀሚድ እንዳሉት በዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ውስጥ የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ ምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው።

በሳይበር ምህዳር ላይ የሚፈጠር እያንዳንዱ ጥቃት ጉዳት እንደሚያመጣ ጠቅሰው ”ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከምንሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ ለሳይበር ደህንነትም ትኩረት መስጠት መሠረታዊ ጉዳይ ነው” ብለዋል።

ለዚህም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞን ለማሳካት ለሳይበር ደህንነት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው ድሬደዋን ‘ስማርት ሲቲ’ ለማድረግ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ለተጀመረው የዲጂታል ጉዞ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

የሳይበር ደህንነት ወር “ቁልፍ መሠረተ ልማት ደህንነት፤ ለዲጂታል ሉአላዊነት” በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት አንድ ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተከበረ ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጪ በአሉ ሲከበር በድሬደዋ የመጀመሪያው መሆኑ ተገልጿል።

በበአሉ ላይ የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደን፣ የአስተዳደሩ ካቢኔ አባላት እና ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አመራር አባላትና ባለሙያዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review