የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዮስ አዲስ ከተሾሙት የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር መንዳይ ሰማያ ኩምባ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
ዶ/ር ጌዲዮን አምባሳደር መንዳይ የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሆነው በመሾማቸው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በቀጣይ በሀገራቱ የጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
አምባሳደር መንዳይ በበኩላቸው በአገራቱ መካከል ያለውን ጠንካራ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
መሰል ጉብኝቶችም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ማስፈን አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፣ ለዚህም በትብብር መስራት እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡