AMN- መጋቢት 8/2017 ዓ.ም
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በነገው ዕለት እንደሚወያዩ ገልጸዋል፡፡
ትራምፕ በትናንትናው ዕለት ኤየር ፎርስ ዋን በተሰኘው ፕሬዚዳንታዊ አውሮፕላን ላይ ሆነው ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፣ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቪላድሚር ፑቲን ጋር ነገ እንደሚወያዩ ተናግረዋል፡፡
በንግግራቸውም በሳምንቱ መጨረሻ ነገ ይፋ ሊደረጉ የሚችሉ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በነገው ዕለት በሚያደርጉት የዩክሬን የሰላም ውይይትም በመሬት እና የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ዙሪያ እንደሚመክሩ ገልጸዋል፡፡
አንዳንድ ንብረቶችን የመከፋፈል ጉዳይን በተመለከተም አስቀድመው ውይይት መጀመራቸውንም አንስተዋል፡፡
ጦርነቱን የማስቆም እድልን በተመለከተ ትራምፕ ሲናገሩ፣ “ምናልባት ሊሳካልንም ላይሳካልንም ይችላል ያሉ ሲሆን፣ እኔ ግን በጣም ጥሩ ዕድል ያለን ይመስለኛል” በማለት ገልጸዋል፡፡
አሜሪካ በዩክሬን የተኩስ አቁም እንዲደረግ ግፊት እያደረገች እንደሆነ እና ነገር ግን ሩሲያ በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ ከመከራከር ይልቅ ግልፅ አቋም አለመስጠቷን አመላክተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የዩክሬን እና የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ሌሊቱን ጥቃት ማድረሳቸውን እንደቀጠሉ የኪዬቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊትሽኮ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኪዬቭ ጥቃት እንደተሰነዘረባት የገለጹት ከንቲባው፣ በደቡባዊ ሩሲያም በዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች በተፈጸመ ጥቃት ጉዳት መድረሱ መዘገቡን ተናግረዋል፡፡
በታምራት ቢሻው