ጃይካ የግብርና ምርትና ምርታማነት በማሳደጉ ረገድ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ገለጸ

You are currently viewing ጃይካ የግብርና ምርትና ምርታማነት በማሳደጉ ረገድ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ገለጸ

AMN – የካቲት 24/2017 ዓ.ም

የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ(ጃይካ) የግብርና ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ እና የግብርና ግብይትን በማጠናከሩ ረገድ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ምክትል ፕሬዚዳንቱ ያማጉቺ ሂሮዩኪ ገልጸዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ምክትል ፕሬዚዳንት ያማጉቺ ሂሮዩኪን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው በግብርናው ዘርፍ ላይ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

በዚህም ጃይካ በሆርቲካልቸር እና በሌሎች የግብርና መስኮች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል በምታደርገው ሂደት ሩዝ በስፋት ማምረት መጀመሯንና በዚህም 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ሀገሪቱ ለሩዝ ልማት ተስማሚ ስነ-ምህዳር ያላት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ጃይካ በሩዝ ልማት ያለውን ልምድ በመጠቀም ምርትና ምርታማነት በማሳደግና ቴክኖሎጂን ከማስፋፋት አኳያ የበለጠ ድጋፍ ያደርግ ዘንድ ጠይቀዋል።

የሩዝ ልማት እሴት መጨመር ጋር በተያያዘ ውስንነት መኖሩን ጠቅሰው፣ በምርት አሰባሰብና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ዶክተር ግርማ 70 በመቶ የሚጠጋው የኢትዮጵያ ኤክስፖርት የግብርና ምርት መሆኑንና ቡና፣ አበባ እና ፍራፍሬ ከፍተኛውን ቦታ እንደሚይዙ ገልጸው የግብርና ግብይትን ለማጠናከር ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ምክትል ፕሬዝዳንት ያማጉቺ ሂሮዩኪ በበኩላቸው፣ የጃይካ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው ኢትዮሼፕ በሆርቲካልቸር እና በሌሎች ሴክተሮች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶአደሮችን ለማበረታታት እንድሁም የሩዝ ልማት ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋት ብሎም የባለድርሻ አካላትን አቅም ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ሂሮዩኪ አብራርተዋል።

በቀጣይም የግብርና ምርትና ምርታማነት ከማሳደግና እንዲሁም የግብርና ግብይትን ከማጠናከር አኳያ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆም ምክትል ፕሬዚዳንቱ መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review