
AMN – ታኅሣሥ -5/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንደስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገበያውን ለማረጋጋት የምርት አቅርቦትን በማስፋት፣ ህገወጥነትን በመከላከልና ህግን በማስከበር ረገድ ጅምር ውጤቶች አሉ ብለዋል፡፡
በከተማዋ ያለውን ገበያ ለማረጋጋትና ለመቆጣጠር የተቋቋመው የግብረ ሀይል የገበያ ማረጋጋት፣ገቢ መሰብሰብ፣ ህገወጥ ንግድ ቁጥጥር ፣ የኢትዮጵያ አዲስ አበባ ታምርት ግብረ ሀይል የ15 ቀናትን የስራ አፈጻጸሙን እና ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት ውይይት አድረጓል።
የግብረ ሀይሉ ሰብሳቢ አቶ ጃንጥራር አባይ በተገኙበት በተካሄደው በዚህ ውይይት ስራዎችን በመገምገምና በተግባር ወርዶ ክትትል በማድረግ፣ ገበያውን ለማረጋጋት የምርት አቅርቦትን በማስፋት፣ ህገወጥነትን በመከላከልና ህግን በማስከበር፣ በኮሊደር ልማት ለሚነሱ ሰዎች መፍትሄ በመስጠት ጥሩ ጅምር እንዳለ አቶ ጃንጥራር ገልጸዋል።
የተቋቋመው ግብረ ሀይል በቀረበው የ15 ቀናት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን አዳጊ አፈጻጸም እንዳለ ተገልቷል፡፡
በስራ ላይ ያጋጠሟቸውን ማነቆዎች ህግ በማስከበር፣ ደረሰኝ ሳይቆርጡ ምርት በሚሸጡ ነጋደዎች፣ underground parking ለምርት ማከማቻ በሚጠቀሙ ነጋደዎች፣ በኮሪደር ልማት ምክንያት የምርት ማከማቻቸው የፈረሰባቸውን ሸማች ማህበራት ምትክ ከመስጠት አንጻር ፣ በመኪና ላይ በሚከናወኑ ሽያጮች፣ የሸገር ዳቦ ምርትን ለማስፋት እና ሌሎች ክፍተቶችን እንዴት መፈታት እንዳለባቸው ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን አቶ ጃንጥራር አባይ ምላሽና የመፍትሄ አቅጣጫ ሰጥተውባቸዋል።
ስራው መናበብን የሚፈልግ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው ግብረ ሀይሉ የሚያደርገው ህግ የማስከበር ስራ እርምጃ መውሰድ ብቻ ሳይሆን አቅርቦትን በማሳለጥና ገበያውን ምቹ ማድረግ መሆኑን አስታውሰዋል ፡፡
እሴት የሚጨምሩ ተቋማትን ማጠናከርና ስርጭቱን ፍትሀዊ በማድረግ ከህረተሰቡ ጋር በመነጋገር በቅርበት መስራት አስፈላጊ ነውም ማለታቸውን የኢንደስትሪ ልማት ቢሮ መረጃያመለክታል።
መጪውን በዓል ህብረተሰቡ በተረጋጋ መልኩ እንዲያሳልፍ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የግብዓቶች ትስስር ማድረግ፣ የገበያ ማእከላትን ለግብይት ምቹ ማድረግ ፣ የግብር አሰባሰቡን ህጋዊ ማድረግ፣ ለሚመጡ ቅሬታዎች አመራሩ አዳማጭና ምላሽ ሰጪ መሆን እንዲሁም የገበያውን ሁኔታ ለህብረተሰቡ መረጃ በመስጠት በቀጣይ በትኩረት እንዲሰሩ አቶ ጃንጥራር አባይ አሳስበዋል ።