AMN ጥር 9/2017 ዓ.ም
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ጎንደር ሦስት ነገሮች ተሸምነው የሠሯት ከተማ መሆኗንና እነሱም እምነት፣ መንግሥት እና ኅብረ ብሔራዊነት መሆናቸውን አስገንዝበዋል ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገሥታቱ ሥርዓተ መንግሥትና አብያተ መንግሥት ማቆማቸውንናየእምነት መሪዎች አብያተ ክርስቲያናትና መስጊዶችን መትከላቸውንም አስታውሰዋል።
እነዚህን ሁለቱን ፍለጋ ከመላ ኢትዮጵያና ከውጭ የመጡ ሰዎች ደግሞ ጎንደርን ኅብረ ብሔራዊት ከተማ አድርገዋታል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጎንደር ጥምቀት በዓል ጎንደር የመንግሥት፣ የቤተ እምነትና የኅብረ ብሔራዊነት ማዕከል በመሆኗ ካቆየቻቸው ዕሴቶቿ አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።
ከጣት ጣት ይበልጣል እንዲሉ አንዳንድ ነገር በአንዳንድ ቦታ እንደሚደምቁና የዘንድሮን የጥምቀት በዓል በጎንደር የሚያከብር ሰው ለጎንደር ትንሣኤ ምስክር መሆኑን አስገንዝበዋል።
ጥንታዊው የፋሲል ግንብ ነባር ይዞታውን ይዞ ታድሷል ፤ ጥንት ወደነበረው ግርማ ሞገስ ተመልሷልም ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ከተማው እንደ ሙሽራ እያበበ መሆኑንና በእውነቱ እነ ዐፄ ፋሲል፣ እነ ዐፄ ቴዎድሮስ ቢመጡ በአድናቆት ከተማቸውን መልሰው መጎብኘታቸው አይቀሬ መሆኑንም ጠቁመዋል ።
የጎንደር ማንሠራራት የኢትዮጵያ ማንሠራራት አንዱ ማሳያ ነውም ብለዋል አቶ ተመስገን በመልእክታቸው ፡፡