ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚያዚያ/ግንቦት 2017 ወር በኢኮኖሚ ልማት፣ ቴክኖሎጂ እድገት፣ አለምአቀፍ ዲፕሎማሲ እና ሀገራዊ ልማት አንፃር የመንግሥታቸውን ፅኑ አቋም የሚያሳዩ ተከታታይ ተግባራት አከናውነዋል

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚያዚያ/ግንቦት 2017 ወር በኢኮኖሚ ልማት፣ ቴክኖሎጂ እድገት፣ አለምአቀፍ ዲፕሎማሲ እና ሀገራዊ ልማት አንፃር የመንግሥታቸውን ፅኑ አቋም የሚያሳዩ ተከታታይ ተግባራት አከናውነዋል

AMN-ግንቦት 24/2017 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚያዚያ/ግንቦት 2017 ወር በኢኮኖሚ ልማት፣ ቴክኖሎጂ እድገት፣ አለምአቀፍ ዲፕሎማሲ እና ሀገራዊ ልማት አንፃር የመንግሥታቸውን ፅኑ አቋም የሚያሳዩ ተከታታይ ተግባራት ማከናወናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የወሩ ተግባር በ44ኛው የሚኒስትሮች ምክርቤት መደበኛ ስብሰባ የጀመረ ሲሆን ቁልፍ የሆኑ ሀገራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ውይይት ተደርጎባቸዋል። ከዚያም በመቀጠል የኢትዮጵያ ታምርት 2017 ኤክስፖ በይፋ ተከፍቷል። ለሶስተኛ ተከታታይ አመት የተከናወነው ኤክስፖ 288 ሀገር በቀል አምራቾች በማደግ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ የአምራች ዘርፍ ምርቶች አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመክፈቻ ንግግራቸው የኢኮኖሚ ሽግግርን አስፈላጊነት አፅንኦት ሰጥተው ያነሱ ሲሆን የሀገር መረጋጋት ከኢኮኖሚ መዘመን ውጭ ሊሳካ እንደማይችል ገልፀዋል። በዘንድሮ አመት የሚጠበቀውን 12 በመቶ እድገት ጨምሮ በዘርፉ የሚጠበቀውን እድገት በማንሳትም የማምረት አቅምን በአግባቡ የመጠቀም ልምምድ መጨመሩን እና የገቢ መጨመርን አዉስተዋል። መንግሥት በግብርና እንደ አግሮ ፕሮሰሲንግ ቴክኖሎጂ የማዘመንን እና ፈጠራን የማበልፀግን ሥራ ቅድሚያ እንደሰጠም በወቅቱ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቴክኖሎጂ እና በዲጂታል ልማት ዘርፍም በ”አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ለአፍሪካ” መርሃግብር የ”ቴክኤክስፖ 2025” ላይ ቁልፍ ንግግር አቅርበዋል።

አፍሪካ ሥነምግባርን በጠበቀ፣ አካታች እና ዘላቂ ባለው የራሷ መንገድ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስን መፃኢ እድገት ቅርፅ የመስጠት እድል እንዳላት አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

እንደ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢንስቲቲዩት፣ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም(ፋይዳ) እና የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ መርሃ ግብርን በማንሳት ኢትዮጵያ የዲጂታል እውቀት የጨበጠ የነገ ትውልድ በመገንባት ላይ ያላትን ሚና ገልጸዋል።

በወሩ አጋማሽም ኢትዮጵያ የID4Afria 2025 ጉባኤን ያስተናገደች ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመድረኩ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓትን የማሻገር አቅም አስረድተዋል:: በአሁኑ ወቅት ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በሥርዓቱ ያቀፈው ፋይዳ ከአሁኑ በፋይናንስ፣ በጤና እና ትምህርት ቁልፍ ዘርፎች በትሪሊዮን ብር የሚቆጠር የዲጂታል ልውውጥ አመቻችቷል።

ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ’Tech Talk with Solomon’ የቃለምልልስ ቆይታም አድርገው ነበር።

በዚሁ ወርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ116ኛው ብሔራዊ የፖሊስ ቀን በዓልም የተገኙ ሲሆን በንግግራቸውም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሊኖር ለሚገባው የቀጠለ ትብብር ጥሪ አቅርበው የፖሊስን የሀገር ሉዓላዊነት እና አንድነት የመጠበቅ ኃላፊነት ደግመው አረጋግጠዋል።

አለምአቀፍ ዲፕሎማሲ የግንቦት ወር ሌላው ትኩረት ነበር። በፓሪስ ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ተገናኝተው የሁለትዮሽ ስምምነቶችን አፈፃፀም ገምግመዋል። እንደ ስቴሽን ኤፍ፣ ኖኪያ ፍራንስ እና የታሌ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ያሉ የቴክኖሎጂ ተቋማትን ጎብኝተው በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ ሳይበር ደኅንነት እና ቴሌኮሚኒኬሽን የታዩ ፈጠራዎችን ተመልክተዋል። እነዚህ ጉብኝቶች ኢትዮጵያ የቀጠናው የቴክኖሎጂ መሪ ለመሆን ያላትን ፍላጎት ያረጋገጡ ነበሩ።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታደሰውን የኖትረዳም ካቴድራል ጎብኝተዋል። ይኽም ኢትዮጵያ እንደ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ባሉ ብሔራዊ ቅርሶች ጥገና ሥራ በማከናወን ላይ ያለችውን የባሕል ጥበቃ ጽኑ አቋም እንቅስቃሴ ተገቢነት ያረጋገጠ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፈረንሳይ ቆይታቸው በመቀጠል ወደ ሮም አቅንተው በጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኒ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ሁለቱ መሪዎች በሁለቱ ሀገራት መካከል የቆየውን የረጅም ዘመን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር እና የኢንቬስትመንት እድሎችን ለማስፋት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ውይይት አድርገዋል።

ጣሊያን በኢትዮጵያ ኢንደስትሪ እና ልማት ዘርፍ ቁልፍ አጋር ሆና ቀጥላለች።

ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ስፔስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲቲዩትን ጎብኝተዋል። በተቋሙ በሥራ ላይ ያለውን የዘመነ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የጂኦስፓሻል መረጃ ለሀገር አቀፍ እቅድ፣ ቅደመ ግምት እና የአደጋ ዝግጁነት ሥራ የሚውልበትን መንገድ ገምግመዋል። ይኽ ጉብኝት መንግሥት በሳይንስ ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ እና በውሂብ መረጃ ላይ የተመሠረተ የአመራር ሥራ ለመከወን ያለውን አፅንኦት ያረጋገጠ ነበር።

በዚሁ ወሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዛት ያላቸው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ውይይቶችን አካሂደዋል። የአንጎላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የፕሬዝደንት ጁአዎ ሎሬንቾን ልዩ መልዕክተኛ ቴቴ አንቶኒዮን ተቀብለዋል። ከእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ሳር ጋርም በተለያዩ መስኮች ትብብሮች የሚጠናከሩበትን መንገዶች ተወያይተዋል። በኳታር ሚኒስትር ዶክተር መሃመድ ቢን አብዱልአዚዝ አልካሊፊ አቅራቢነት ከኳታር አሚር የተላከውን መልዕክትም ተቀብለዋል።

በአጠቃላይም በሚያዚያ/ግንቦት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ዘርፎች ሰፋ ያሉ ክንውኖች ያካሄዱበት፣ በሀገር ውስጥ ትርጉም ያላቸው ርምጃዎች የተከናወኑበት፣ በዲጂታል እና ፈጠራ መስክ እመርታዎች የተመዘገቡበት ብሎም በአለምአቀፍ መድረኮች ትብብሮች የተጠናከሩበት ወር ነበር።

ሁሉም ተግባራት ለኢትዮጵያ እድገት እና አለምአቀፍ ግንኙነት የታለሙ ስኬታማ ክንውኖች እንደነበሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review