
AMN- ኅዳር 11/2017 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ የተገነባውን ኢትኖ ማይኒንግ የወርቅ ፋብሪካ መርቀው ከፍተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት፣ ኢትኖ ማይኒንግ የአኮቦ ሚኒራልስ ኩባንያ መጋቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትኖ ማይኒንግ በስካንዲኔቪያን ሀገራት መሠረቱን ያደረገ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኩል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ወርቅ ፍለጋ እና ማውጫ ላይ የተሰማራ ኩባንያ መሆኑንም ጠቁመዋል።
“በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ በተደረገው በዚህ ትርጉም ባለው ኢንቨስትመንት ሁላችንም እንኳን ደስ አለን ለማለት እንፈልጋለን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ባለፉት ሶስት አስርት አመታት በዲማ ወረዳ የምትገኘው ዲማ ከተማ በአነስተኛ ባሕላዊ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ሂደት ላይ ብዙውን ጊዜ ብክነት የተሞላበት አሠራር በተግባር የተቆየባት ከተማ መሆኗን አንስተዋል።
ይኽ አዲስ ኢንቨስትመንት በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ እና ደረጃውን የጠበቀ የወርቅ ምርት ከማስገኘቱም በላይ በሕገወጥ የማዕድን ሥራ ለተጋረጠው ፈተና ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ከዚህም ባሻገር ለጋምቤላ ክልል ዘላቂ ልማት በክልሉ ያለውን እምቅ ሀብት ለሕዝቡ እና ለክልሉ ጠቀሜታ የማዋል ያለውንም ተነሳሽነት ያሳያል ነው ያሉት።