AMN – መጋቢት 9/2017 ዓ.ም
ጠንካራ ፓርቲ የመገንባት ርብርባችን በሁለንተናዊ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ገለጹ፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ተሻሽሎ በሚፀድቀው የአደረጃጀት አሰራር መመሪያ እና በፓርቲ ስራዎች ወቅታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ፣ አዳዲስ መመሪያዎች የሚወጡት፣ ነባር መመሪያዎች የሚሻሻሉት እንዲሁም የተለያዩ አደረጃጀቶች የሚፈጠሩት ወቅቱን በሚመጥን ብቃት እና ዝግጁነት ተልዕኮን በስኬት ለመወጣት መሆኑን አስገንዝበዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ህገ ደንብን መሰረት በማድረግ የተዘጋጀው የአደረጃጀት እና አሰራር መመሪያው ጠንካራ ፓርቲ ለመገንባት ለሚደረገው ርብርብ ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን በየደረጃው የሚገኘው አመራር የሚሰጣቸው የሀሳብ ግብአቶች ተጨማሪ አቅም መሆናቸውንም አስረድተዋል።
ወቅታዊ የፖለቲካ ስራ እንቅስቃሴዎችም የተመከረባቸው ሲሆን፣ የጠራ አመለካከት፣ ግልፅ አሰራር፣ ቁርጠኛ አፈፃፀምን በማዳበር የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል እየተደረገ የሚገኘውን ርብርብ ማጠናከር እንደሚገባም አቶ ሞገስ አሳስበዋል።
ተከታታይነት ባለው የእርስ በእርስ መገነባባት፣ ብልሹ አሰራሮችን በመታጋል፣ መዘናጋትን በማስወገድ፣ የተጠያቂነት አሰራርን በማስፈን የጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ርብርቡን ማጠናከር እንደሚገባም አቶ ሞገስ አቅጣጫ መስጠታቸውን ከጽሕፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።