AMN – የካቲት 9/2017 ዓ.ም
ባርባዶስ የካሪቢያን ባህር ውስጥ የምትገኝ ደሴት ስትሆን ዋና ከተማዋ ብሪጅታውን (Bridgetown) ይባላል፡፡
ባርባዶስ በአትላንቲክ በነበረው የባሪያ ንግድ ምክንያት ከአፍሪካ ጋር ጥልቅ ታሪካዊ ትስስር አላት።
በ17ኛው እና በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በባርነት የተያዙ አፍሪካውያን በስኳር ልማት ላይ ለመስራት ወደ ባርባዶስ በግዳጅ ይወሰዱ ነበር።
አብዛኛዎቹ እነዚህ በባርነት የተያዙ ግለሰቦች ከምዕራብ አፍሪካ የተጋዙም ነበሩ።
ከዘመናት ባርነት እና ቅኝ ግዛት በኋላም በባርነት የሄዱት አፍሪካውያን ያሳደሩት ባህላዊ ተጽእኖ በባርቤዲያን ባህል ውስጥ ጉልህ ስፍራ አስቀምጧል።
በማንም ቅኝ ያልተገዛችው እና የአፍሪካውያን የነጻነት እና የኩራት ምልክት ተደርጋ የምትታየው ኢትዮጵያም በጥቁሮች ነፃነት በፓን አፍሪካ ንቅናቄ ውስጥ ጉልህ ሚና ስታደርግ ቆይታለች ።
ይህ ሚናዋ በአፍሪካውያንን ብቻ ሳይሆን በባርቤዶስ ያሉ አፍሮ-ካሪቢያን ህዝቦችም ጭምር ልዩ ቦታ አለው።

በፓን አፍሪካን እንቅስቃሴ ለባርባዶሳውያንና በመላው ዓለም ላሉ አፍሪካውያን ተምሳሌት ተደርገው ይነሳሉ።
ከፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ባለፈ ቅኝ ግዛትን አሻፈረኝ ብላ ነፃነቷን ጠብቃ የቆየችውና ወራሪዎችን በአድዋ ድባቅ በመምታት በተቀዳጀችው ድል የምትታወቀው ሀገራችን በባርባዶሳውያን ዘንድ ልዩ ቦታ አላት ፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኩራትና የነፃነት ፋና ሆኖ ባርባዶስን ጨምሮ በአፍሮ ካሪቢያን ማንነት ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ችላለች።
እነዚህ ታሪካዊ ሁነቶችም የባርባዶስ-አፍሪካና ኢትዮጵያ ግንኙነት ዋና ማጠንጠኛዎች መሆናቸውን የዳሰስናቸው ማህበራዊ የትስስር ገፆች ያመለክታሉ ፡፡
የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት ርእሰ ጉዳይ የማካካሻ ፍትህ ለአፍሪካውያንና ዘርዐ አፍሪካውያን የሚል መሆኑ ይታወቃል ፡፡