AMN – የካቲት 6/2017 ዓ.ም
የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ የህብረቱ ዋና መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል። ከጉባኤው ጋር በተያያዘ የአፍሪካ ህብረት የትስስር ገፆች ተከታዮቹን መረጃዎች አጋርተውናል፦
46ኛው የአፍሪካ ኅብረት ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ከየካቲት 5 ቀን ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 8 እና 9 ይካሄዳል፡፡
ጉባኤው “የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካዊያንና ዘርዓ-አፍሪካዊያን” በሚል መርህ እየተካሄደ ነው፡፡
የአፍሪካ ህብረት 55 አባል ሀገራትን ያቀፈ ነው ፡፡
በዘንድሮው ጉባኤ 49 አባል ሀገራት እየተሳተፉበት ይገኛል፡፡
ማሊ ፣ ሱዳን ፣ ጊኒ ፣ ቡርኪናፋሶ ፣ ሶማሌላንድ እና ኤርትራ በአጠቃላይ ስድስት የአፍሪካ ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች በጉባኤው አልተገኙም

የጉባኤው አጀንዳ እና የትኩረት አቅጣጫዎች
የመሪዎች ጉባኤው በአፍሪካ ልማት ላይ ያተኮሩ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ማለትም በትምህርት፣ በጤና፣ በሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ይወያያል ፡፡
1. በትምህርት ፣ ለአፍሪካውያን ሁሉን አቀፍ እና ጥራት ያለው የትምህርት እድሎችን በማቅረብ እንዲሁም ጠንካራ የትምህርት ሥርዓት በመዘርጋት ላይ ይወያያል፡፡
2. በጤናው ረገድም በአፍሪካ የወባ ቁጥጥርን በማጠናከር እና በማጥፋት ረገድ የተደቀኑ ፈተናዎች ላይ ይመክራል
3. በሰላምና ፀጥታ ረገድም የግጭት እና ጽንፈኝነት መንስኤ የሆኑትን እንደ ምዕራብ አፍሪካ የባህር ዳርቻ እና ሞዛምቢክ ያሉ አካባቢዎች ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት የውይይቱ አካል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በሽመልስ ታደሰ