ሪቻርድ ቪ ቡርካሸር “የደች በሽታን ማከም” (Curing the Dutch Disease) የተሰኘ ጥናታዊ መፅሐፍ እ.ኤ.አ በ1996 አሳትመዋል፡፡ በዚህ ጥናታዊ መፅሐፋቸው ኔዘርላንድስ በብዙ መልኩ የበለፀገች ብትሆንም በአንድ ኢኮኖሚ ምንጭ ላይ በመተማመኗ የውድቀትን ካባ ለመከናነብ ተገዳ እንደነበርም አብራርተዋል። ኔዘርላንድስ እ.ኤ.አ. በ1950 ግሮኒንገን በተባለ ግዛቷ ትልቅ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አገኘች፡፡ ይህ የተፈጥሮ በረከት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ማርሽ ቀያሪ ሆኖ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ የተፈጥሮ ጋዝ ከኔዘርላንድስ አጠቃላይ ምርት ውስጥ 40 በመቶው እና ከኤክስፖርት ገቢው ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ያዘ። ከተፈጥሮ ጋዝ የሚገኘው ገቢ የኔዘርላንድስን መንግሥት በመሠረተ ልማት እና በልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ልማቶች ላይ እንዳሻው መዋዕለ ነዋይ ፈሰስ እንዲያደርግ አስቻለው። የሀገሪቱንም ገጽታ ከፍ አደረገው። ይሁን እንጂ ኔዘርላንድስ በተፈጥሮ ጋዝ ላይ ከመጠን በላይ መመካቷ ሀገሪቱን ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አጋለጣት፡፡
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ቪ ቡርካሸር ጥናታዊ መፅሐፍ መሠረት፣ እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ ኔዘርላንድስ ብዝሃ የኢኮኖሚ ስልትን መከተል ባለመቻሏ ኢኮኖሚዋ ተዳከመ፡፡ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷ ቀነሰ፤ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችም ተጋለጠች፡፡ ሀገራት በአንድ የኢኮኖሚ ምንጭ ላይ ከመጠን በላይ ሙጥኝ ካሉ ውድቀትን እንደሚያመጣ ማሳያ ሆነች፡፡ ስለዚህ አለም ከዚህ ትምህርት በመውሰድ በአንድ ኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ ከተንጠለጠለ የኢኮኖሚ አቅጣጫ በመውጣት ብዝሃ ኢኮኖሚን መከተል እንዳለበት መገንዘብ ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያም ይህንን እውነታ በውል በመረዳት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርና እና መሰል ጥቂት ዘርፎች ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የነበረውን የኢኮኖሚ እይታ አድማሱን በማስፋት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም አድርጋለች። ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን እና አይሲቲ አምስቱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ምሰሶዎች ሆነው ተቀረፁ፡፡ ይህንንም ተከትሎ እየተሰራ ባለው ስራ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ስለመሆኑ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ይንገስ አለሙ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ገቢራዊ ከመደረጉ ከ2011 ዓ.ም በፊት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተከታታይ እድገት የነበረው ቢሆንም በጥቅሉ ሲመዘን የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ይስተዋልበት እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ። ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ምንጭን በማስፋት የብዝኃ-ኢኮኖሚ አተያይ እንዲኖርና ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን እና አይ.ሲ.ቲ ዘርፎች ላይ በልዩ ትኩረት የተሰራው ሥራ ውጤት ማምጣቱን ይንገስ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
በዚህ ዘርፍ ላይ የተደረገው ማሻሻያ በተለይም ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የውጭ ንግድ አፈጻጸምን በማሳደግ የንግድ ሚዛኑን ከማሻሻል በተጨማሪ የሀገሪቱ ገቢ እንዲያድግና የዕዳ ክፍያ በተገቢው መልኩ እንዲካሄድ ስለመደረጉም እያየን ነው ብለዋል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ሐሳብ ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት ካካሄደ በኋላ ባወጣው የአቋም መግለጫ፣ ሕልማችን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን እውን በማድረግ የሀገራችንን ብልጽግና ማረጋገጥ ነው። ረጅም በማይባል ጊዜ ውስጥ ጠንካራና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ የገነባች ሀገር ማየትን በእጅጉ እንሻለን። የሚል መልዕክት ያዘለ ነጥብ አስፍሯል፡፡
ኢኮኖሚው ነባር አቅሞችን የሚያጠናክር፣ ወደ አዳዲስ ዘርፎች የሚሸጋገርና ወደ መጪው ዘመን የፈጠራ ኢኮኖሚ የሚያስፈነጥር እንዲሆን በውጤታማነት ለመታገል ስለመወሰኑም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታትም የተቃና የኢኮኖሚ ማዕቀፍ በመገንባት ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና ዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ተደምሮ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር በማምጣት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ያስችል ዘንድ በመፍጠር፣ በመፍጠንና በማላቅ እንሠራለንም ሲል ያትታል የአቋም መግለጫው፡፡
ለመሆኑ በኢትዮጵያ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማድረግ የሚያስችሉ ምን ተግባራት ተከናውነዋል የሚል ጥያቄ ያነሳንላቸው ይንገስ (ዶ/ር) በሰጡን ማብራሪያ፣ ለአብነትም የብዝሃ ኢኮኖሚ ፖሊሲን በመከተል በግብርና በተለይም በበጋ ስንዴ እና በቱሪዝም ዘርፎች በርካታ ለውጦች ስለመመዝገባቸው ጠቅሰው፣ እነዚህና መሰል ውጤቶች ለመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግሩ መሠረት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ ይንገስ (ዶ/ር) ገለፃ፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በበጋ መስኖም ሆነ በሁሉም ምርት ወቅቶች በተለይም በስንዴ ምርት እያመጣችው ያለው ለውጥ ከሀገር አልፎ ለአፍሪካም አዲስ ተስፋን አመላካችና ተምሳሌት የሚሆን ነው፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ባለፉት ስድስት ዓመታት በስንዴ ልማት ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራር በመውጣት በዕውቀት እና በእቅድ በተሰራው ስራ እመርታዊ ለውጥ መገኘቱን ተናግረዋል። በዚህም ስንዴን ከውጭ ከማስገባት ወጥተን ወደ ውጭ እስከመላክ መድረሳችን በተግባር የታየ ውጤት ነው ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግና የተፈጥሮ ጸጋን ወደ ልማት ምንጭ በመቀየር ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የምጣኔ ሀብት መምህሩ ይንገስ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡
እንደ ሀገር ለረጅም ዓመታት በግብርና ላይ ተመስርቶ የቆየውን የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ ወደ ብዝሃ ዘርፍ መቀየሩ ትልቅ እምርታ መሆኑን ያስታወሱት የምጣኔ ሀብት መምህሩ፣ በዚህም በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በዲጂታል ዘርፉ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመሰራቱ የተሻለ ለውጥ እየተመዘገበ በመሆኑ ይህንኑ ግለቱን በጠበቀ መልኩ ማስቀጠል መዋቅራዊ ሽግግሩን እውን ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡
ይንገስ (ዶ/ር) በግብርናው ዘርፍ ያሉንን አቅሞች አሟጥጦ ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት፣ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ያሉ መሬቶች ጦም እንዳያድሩ በበጋም በክረምትም እንዲያመርቱ እየተደረገ ያለው ርብርብ በተለይም በመስኖ ላይ የመጡ ለውጦች የበለጠ ተጠናክረው መቀጠል ከቻሉ እንደ ሀገር ከራስ አልፎ ለሌሎቹም የሚተርፍ አቅም አለን፡፡

የቱሪዝሙን ዘርፍ በማጠናከር መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ሂደቱን በእጅጉ የሚያግዙ ተግባራት መከናወናቸውን የጠቀሱት ይንገስ (ዶ/ር)፣ በተለይ በገበታ ለሸገር፣ ገበታ
ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ በተሰኙ
ፕሮጀክቶች በርካታ ሀብቶች መፈጠራቸውን ገልፀዋል፡፡ አክለውም፣ በእነዚህ ፕሮጀክቶች የተገነቡት ወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም፣ ሃላላ ኬላ ሪዞርት፣ ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት፣ ቤኑና መንደር፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥም እንደ እንጦጦ ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ አንድነት ፓርክ፣ እንዲሁም በኮሪደር ልማት ስራው የተፈጠሩ እሴቶች
የቱሪዝም አቅምን አጎልብተዋል፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግሩን ያፋጥናል ብለዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ረገድም አበረታች ውጤቶች መምጣታቸውን የሚናገሩት ይንገስ (ዶ/ር)፣ በተለይ ኢትዮጵያ ታምርት የተሰኘው ንቅናቄ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ ሌሎች አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማነቃቃት በኢኮኖሚው ዘርፍ ውጤት ማስገኘታቸውን ገልጸው፣ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ሲደረግ የቆየው ጥረትም መልካም ውጤት የታየበት ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታው ሳይንስና ቴክኖሎጂን በማስፋፋት የብዝሃ ኢኮኖሚ ስርዓቱ የበለጠ የተጠናከረና ዘላቂነት ያለው ዕድገት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ገልጸዋል። የኢፌዴሪ ፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ሀገራዊ ሪፎርሙን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለፁት፣ በሪፎርሙ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ኢትዮጵያን በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ካስመዘገቡ ሀገራት ተርታ ማሰለፍ ተችሏል። ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአማካይ 7 ነጥብ 2 በመቶ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች፡፡ በዚህም ከምስራቅ አፍሪካ ትልቁን ምጣኔ ሃብት የገነባች ሀገር መሆን ችላለች፡፡
በማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራና በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች መመዝገባቸውን ያነሱት ሚኒስትሯ፣ በተለይም በግብርና፣ በማዕድን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝም፣
በዲጂታል ልማትና ሌሎች ዘርፎችም ከፍተኛ እድገትና ስኬት እየተገኘ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በንግድና ኢንቨስትመንት መስክም የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን የሚያበረታቱ ስራዎች ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ በገንዘብ ፖሊሲም ከዚህ በፊት የነበረውን ጉድለት መሙላት ያስቻሉ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል። የገቢ መጠንን በማሳደግ ረገድም ከፍተኛ እድገትና መሻሻል ማሳየት የተቻለበት አጋጣሚ መፈጠሩን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ትርፋማነትም እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በመስኖ ልማት ስራ በተለይም በበጋ መስኖ ልማት ባለፈው ዓመት ብቻ 230 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት መገኘቱን የገለፁት ሚኒስትሯ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታም ባለፉት ስድስት ዓመታት 27 ሺህ ኪሎ ሜትር አዲስ የመንገድ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ ሀገር እየተከናወኑ ካሉት ከእነዚህ ክንውኖች አንፃር ኢትዮጵያ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን ለማድረግ የተያያዘችው ጉዞ እውን የሚሆን ስለመሆኑ የምጣኔያዊ ሀብት መምህር ይንገስ (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡ ከሚታዩ ውጤቶች አንፃር ሲመዘን በርግጥም የኢትዮጵያ ብልፅግና አይቀሬ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል፡፡
በጥቅሉ ተከታታይና ዘለቄታ ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲመጣ አምስቱ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ምሶሶዎች በቴክኖሎጂ መተሳሰር እንዳለባቸው የጠቆሙት ይንገስ (ዶ/ር)፣ ይህም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ያለው መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር በሚፈለገው ፍጥነትና የጥራት ደረጃ እንዲረጋገጥ ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመለሰ ተሰጋ